ጥቅስ

ጌታዬ
እግዚአብሔር ሆይ
እስከዚህ ያደረስኸኝ
እኔ ማን ነኝ ?
ቤቴስ ምንድር ነው?
2 ሳሙ 7፥18

Saturday 16 March 2013

አርባ መአልትና አርባ ሌሊት ጾመ ማቴ.4፥2

አርባ መአልትና አርባ ሌሊት ጾመ ማቴ.4፥2 አትም ኢሜይል

የካቲት 29/2004 ዓ.ም.
በመ/ር ምሥጢረሥላሴ ማናየ
ይህ ከላይ ያነሣነው ርዕስ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችንና አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አርባ መአልትና አርባ ሌሊት መጾሙን ያስተምረናል፡፡
በዚህ ኀይለ ቃል ሁለት ታላላቅ ቁም ነገሮችን ቃላትን እንመለከታለን
  1. አርባ መአልትና አርባ ሌሊት
  2. ጾም የሚሉት ናቸው፡፡

በቅድሚያ አርባ መአልትና አርባ ሌሊት የሚለውን ከእነ ምስጢሩ እንመለከተዋለን፡፡ ቀጥለን ደግሞ ጌታችንስ ለምን አርባ መአልትና አርባ ሌሊት ጾመ? የሚለውን እንመለከታለን እግዚአብሔር አይነልቡናችንን ይክፈትልን፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን የፈጠረውን የሰው ልጆችን አባት አዳምን፣ በልጅነት አክብሮ ገነት ያስገባው በፈጠረው በአርባ ቀኑ ነው፡፡ “ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ እግዚአብሔር ዘገብሮ ለአዳም” አዳምን የፈጠረ እግዚአብሔር ቅዱስ ነው እያሉ እያመሰገኑ መላእክት ወደገነት አስገብተውታል /ቀሌ.4፥/

“ወላምድኅረ ተፈጸመ ለአዳም ፵ መዋዕል በምድር ኀበ ተፈጥረ አባዕናሁ ውስተ ገነተ ኤዶም ኩፋ.9፥12 ለአዳም አርባ ቀን ከተፈጸመለት በኋላ ወደገነት አስገባነው፡፡ ሔዋንንም በሁለት አርባ ማለትም በሰማኒያ ቀኑዋ ወደገነት አስገቧት ኩፋ.4፥12

በተጨማሪም አዳም ትእዛዘ እግዚአብሔር ካፈረሰ በኋላ ዲያብሎስ በአቋራጭ መጥቶ አስወጣው እንጂ ሱባኤ የገባው ለአርባ ቀናት ነበር፡፡ ይህን አርባ ቀን የሰው ልጆች ከስህተት በኋላ በቀንም ሆነ በዓመት ለጾም፣ ለሱባኤ፣ ከዚያ አልፎ ለመቅጫነት አግልሏል፡፡

Monday 11 March 2013

ወደ ቤቴል ውጣ በዚያም ኑር ዘፍ.35፥1

ወደ ቤቴል ውጣ በዚያም ኑር ዘፍ.35፥1 አትም ኢሜይል

የካቲት 27 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዲ/ን ሰለሞን መኩሪያ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ
ይህንን የተናገረ አምላካችን እግዚአብሔር ነው፡፡ ይህ የተነገረው እስራኤል ለተባለ ያዕቆብ ነው፡፡
በቅዱስ መጽሐፍ ታሪኩ ተጽፎ እንደምናገኘው ከወንድሙ ከዔሳው ሸሽቶ የአባቱን የይስሐቅን በረከት ተቀብሎ ወደ አጎቱ ወደ ላባ ሲሄድ ሎዛ ከምትባለው ምድር ሲደርስ ጊዜው መሸ፡፡ እርሱም ደክሞት ስለነበር ድንጋይ ተንተርሶ ተኝቶ ሳለ ሌሊት በራእይ እግዚአብሔር ተገለጠለት ራእዩም የወርቅ መሰላል ከምድር እስከ ሰማይ ተተክሎ በመሰላሉ መላእክት ሲወጡ ሲወርዱ ነበር፡፡ እግዚአብሔርም በዙፋኑ ተቀምጦ ነበር፡፡ ያዕቆብንም “እኔ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅ አምላክ እግዚአብሔር ነኝ፤ አትፍራ፣ ይህችን አንተ የተኛህባትን ምድር ለአንተም ለዘርህም እሰጣለሁ ዘርህም እንደ ባሕር አሸዋ ይሆናል፡፡ በአንተ በዘርህ አሕዛብ ይባረካሉ፡፡ እነሆም እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፡፡ የነገርኩህን ሁሉ እስካደርግልህ ድረስ አልተውህም” አለው፡፡ ያዕቆብም ከእንቅልፍ ተነሥቶ በእውነት እግዚአብሔር በዚህ ስፍራ አለ፤ እኔ አላወቅሁም ነበር፡፡ ይህ ሥፍራ እንዴት ያስፈራል? ይህ ስፍራ የእግዚአብሔር ቤት ነው እንጂ ሌላ አይደለም፤ ይህችም የሰማይ ደጅ ናት፡፡ ያዕቆብም ማልዶ ተነሣ ተንተርሷት የነበረችውንም ድንጋይ ወስዶ ሐውልት አድርጎ አቆማት፤ በላይዋም ዘይት አፈሰሰባት፡፡ ያዕቆብም ያን ሥፍራ ቤቴል ብሎ ጠራው አስቀድሞ ግን የዚያ ከተማ ስም ሎዛ ነበር፡፡ ያዕቆብም ስዕለትን ተሳለ፡፡ እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ቢሆን በምሄድበት መንገድ ቢጠብቀኝ፣ የምበላውን እንጀራ የምለብሰውን ልብስ ቢሰጠኝ ወደ አባቴ አገር በሰላም ቢመልሰኝ እግዚአብሔር አምላኬ ይሆንልኛል፡፡ ለሐውልት ያቆምኳት ይህች ድንጋይ የእግዚአብሔር ቤት ትሆንልኛለች፤ ከሰጠኸኝ ሁሉ ለአንተ ከአስር እጅ አንዱን እሰጥሃለሁ አለ፡፡ እግዚአብሔርም ስእለቱን ሰምቶ ሁሉንም ፈጸመለት ወደ አጎቱ ወደ ላባ ደርሶ ሚስት አግብቶ ብዙ ልጆችን ወልዶ እንዲሁም ብዙ ባሮችን እና ሀብት ንብረት አፍርቶ ወደ አባቱ ሀገር ሲመለስ እግዚአብሔር አምላክ ተገለጠለትና “ወደ ቤቴል ውጣ በዚያም ኑር” ብሎ አዘዘው ዘፍ.28፥10-20፣ ዘፍ.35፥1፡፡
ለመሆኑ ይህች ቤቴል ማን ናት? እግዚአብሔር አምላክ ለጊዜው ያዕቆብና ቤተሰቡ እንዲኖሩባት ለፍጻሜው ሁላችንም እንድንኖርባት የታዘዝንባት ቤቴል ምስጢራዊ ትርጉሟ ምን ይመስላል? አባቶቻችን እንዲህ ይተረጉሙታል፡፡