፩፦ መጠናናት፤
ምንም እንኳን የሰው ልጅ ተጠንቶ የማያልቅ ሳይንስ ቢሆንም ፦ ወደ ትዳር ዓለም ከመግባት በፊት ፦እንደ ሰው፥ በሰው አቅም መጠናናት እንደሚያስፈልግ ለማንም ግልጥ ነው። ይኸውም በሰከነ ልቡና ፥ በተረጋጋ መንፈስ ሊሆን ይገባል። በትውውቅ ሰሞን የተሸፈነ ብዙ ነገር ፥ በሂደት ቀስ እያለ ብቅ ማለቱ ስለማይቀር ጊዜ መስጠት ያስፈልጋል። ሰውን የምናጠናው ድካም የሌለበት ፍጹም የሆነ ሰው ለማግኘት አይደለም። ምክንያቱም እኛም ፍጹም አይደለንምና ነው ፥ አንድም በዓለመ ሥጋ ፍጹም ሰው አይገኝምና ነው። በመሆኑም፦ በእኛ ዘንድ ድካም እንዳለ ሁሉ ፦ በሌላም በኲል ድካም ሊኖር እንደሚችል አምነን ኅሊናችንን ልናዘጋጀው ይገባል። ከዚ ህ በኋላ ድካሙን ፦ በአራት ደረጃ ከፍለን ልናየው እንችላለን። ፩ኛ፦ በቶሎ የሚወገድ ድካም ፤ ፪ኛ ፦ በሂደት የሚወገድ ድካም፤ ፫ኛ፦ ልንሸከመው የሚገባን ድካም፤ ፬ኛ ፦ የማይወገድ ድካም፤
፩፥፩፦ በቶሎ የሚወገድ ድካም፤
የሰው ልጅ በትምህርት ፥ በምክርና በተግሣጽ ፦ ከጥፋቱ ሊመለስ ፥ ከድካሙም ሊበረታ ይችላል። ስለሆነም ያሉትን ደካማ ጐኖች ዘርዝሮ በማውጣት ፦ እርስ በርስ መነጋገር ፥ መማማር ያስፈልጋል። ከአቅም በላይ የሆነውን ደግሞ ወደ ካህኑ በማምጣት ማስ መከር ይገባል። እንዲህ ዓይነቱ ድካም ፦ ከእውቀት ማነስ፥ ከመካሪ ማጣት ፥ አርአያ የሚሆን ሰው ካለማግኘት በመሆኑ በቶሎ ይወ ገዳል። ጠቢቡ ሰሎሞን፦ «ምክር በሰው ልቡና እንደ ጥልቅ ውኃ ነው፤ አእምሮ ያለው ሰው ግን ይቀዳዋል።» እንዳለ፦ አእምሮ ያላቸው የሚያስተውሉ ሰዎች ይስተካከሉበታል። ምሳ ፳፥፭። «ተግሣጽን የሚወድድ ዕውቀትን ይወድዳል፤» እንዲል፦ በሁሉ ይገሠጻሉ። ምሳ ፲፪፥፩። «የተማረ ልጅ ብልህ ይሆናል፤» እንዲል፦ ልባሞች ፥ አስተዋዮች እየሆኑ ይሄዳሉ። ምሳ ፲፥፭። ይህም ከምድራዊ ሀብት የሚበልጥ ሀብት ነው። ምክንያቱም « ከብር ይልቅ ትምህርትን ፥ ከተፈተነ ወርቅም ይልቅ ዕውቀትን ተቀበሉ ፤ » ይላልና። ምሳ ፰፥፲። «ትምህርትና ተግሣጽም የሕይወት መንገድ ነውና፤» የሚልም አለ። ምሳ ፮፥፳፫።