ጥቅስ

ጌታዬ
እግዚአብሔር ሆይ
እስከዚህ ያደረስኸኝ
እኔ ማን ነኝ ?
ቤቴስ ምንድር ነው?
2 ሳሙ 7፥18

Thursday 31 January 2013

ዕረፍታ ለእግዝእትነ ቅድስት ድንግል ማርያም (ጥር 21)


ማርያም ማለት መርሕ ለመንግሥተ ሰማያት ማለት ነው፡፡ ምዕመናንን እየመራች ወደ መንግስተ ሰማያት ታስገባለችና፡፡ አንድም ፍጽምት ማለት ነው፡፡ በሥጋም በልቦናም ንጽሕት ናትና፡፡ ማርያም ማለት ልዕልት ማለት ነው፡፡ ከፍጡራን በላይ ናትና፡፡ ‹‹ማር›› በምድር ‹‹ያም›› በሰማይ ናት፡፡ ማር በምድር ተወዳዳሪ የሌለው ምግብ ነው፡፡ ያም በሰማይ ቅዱሳን የሚመገቡት በብሔረ ሕያዋን በብሔረ ብፁዓን ያሉ ቅዱሳን የሚመገቡት ጣፋጭ ምግብ ነው፡፡ የእመቤታችን ርህራሄዋ በምድርም በሰማይም ሁሉ ጣፋጭ ነውና ማርያም ተባለች፡፡እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህ ምድር ላይ 64 ዓመት ኖራ ጥር 21 እሑድ ቀን ጌታ እልፍ አእላፍ መላእክቱን አስከትሎ መጥቶ እናቴ ሆይ ከዚህ ዓለም ድካም ላሳርፍሽ መጣሁ ቢላት ልጄ ሰማይና ምድር የማይወስኑህን ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማኅፀኔ ተሸክሜ፣ በድንግልና ወልጄህ እሞታለሁን? አለችው፡፡ በሲኦል የሚሰቃዩ ነፍሳትን አሳይቶ እናቴ ሆይ ሞትሽ ለእኚህ ቤዛ ይሆናቸዋል አላት፡፡ እመቤታችንም እኚህን ከማርክልኝስ ይሁን አለችው፡፡ ቅድስት ሥጋዋንም ለይቶ በቃለ አቅርንት በዝማሬ መላእክት አሳረጓት፡፡ ደቀመዛሙርቱንም ከያሉበት ደመና ጠቅሶ ካለችበት አድርሶ እመቤታችሁን ቅበሩ አላቸው፡፡ በአጎበር አድርገውም ይዘዋት ወደ ጌቴሴማኒ ሲወስዷት አይሁድ አይተው ልጅዋን ተነሣ ዐረገ እያሉ ሲያውኩን ይኖራሉ፤ አሁን ደግሞ እሷን ዐረገች ተነሣች እያሉ ሊያውኩን አይደለምን ኑ የማርያምን ሥጋ እናቃጥል ብለው ተነሡ፡፡ ከመካከላቸው አንዱ ታውፋንያ ዘሎ የአልጋውን ሸንኮር ቢይዘው የታዘዘ መልአክ መጥቶ ሁለት እጁን በሰይፍ ቀላው፡፡ በድያለሁ ማረኝ ብሎ ቢማፀናት እራሷን ዘንበል አድርጋ ቅዱስ ጴጥሮስን እንደነበረው አድርግለት አለችው፡፡ ቢመልሰውም ድኖለታል፡፡ ከዚህ በኋላ ዮሐንስን ጨምሮ ከመካከላቸው ነጥቆ ገነት በዕፀ ሕይወት ሥር አኑሯታል፡፡

ድንግል እመቤት ንጹሕት ምሕረት
ለሁሉ ምታዝን ርኅርኅት እናት
የአምላክ እናት ሁና እንደምን ትሙት፡፡
ድንግል በሥጋዋ ሞትን ስትቀምሰው
ሲዘምሩ ዋሉ ነፍሳት ተደስተው
በሞቷ ቤዛነት ለዘለዓለም ድነው፡፡
የእመቤቴ ነፍሷን ጌታ ሲያሳርጋት
መላእክት ከሰማይ ከምድር ሐዋርያት
መጡ እየዘመሩ በጥዑም ማኅሌት
ለሰሚ እስኪመስል የደረሰ ምጽአት
እመቤቴ ማርያም አማልደሽ ከልጅሽ
እድሜን ለንስሓ ስጭኝ እባክሽ
አንቺኑ ነውና ተስፋ ያረግሁሽ
ቅዱስ ያሬድ

የእናታችን የእመቤታችን ቅድስት ማርያም ልመናዋ ምልጃዋ ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይኑር፡፡
በሰንበት ት/ቤቱ ትምህርት ክፍል
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

No comments:

Post a Comment