ጥቅስ

ጌታዬ
እግዚአብሔር ሆይ
እስከዚህ ያደረስኸኝ
እኔ ማን ነኝ ?
ቤቴስ ምንድር ነው?
2 ሳሙ 7፥18

Sunday 3 November 2013

ምሥጢረ ንስሐ


 ምሥጢረ ንስሐ
ንስሐ ፦ ነስሐ ተፀፀተ ካለው የተገኘ ሲሆን ፤ ንስሐ ማለት በሠሩት ኃጢአት መፀፀት ፣ ማዘን ፣ ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ መወሰን ፤ ማለት ነው ። ንስሐ ከዘለዓለማዊ ፍርድ የሚያድን ፤ ዘማዊውን እንደ ድንግል ፤ ሌባውን መጽዋች የሚያደርግ በፊት ከተሠራው ኃጢአት ንጹህ አድርጎ ፤ ከእግዚአብሔር ጋር አንድ የሚያደርግ  ምሥጢር ነው ።
ንስሐ ፦ ከንስሐ በፊት ፣ በንስሐ ጊዜ ፣ ከንስሐ በኋላ፤ ተብሎ  በሶስት ይከፈላል
ከንስሐ በፊት
1 መፀፀት ፤ አንድ ክርስቲያን በድፍረትም ይሁን በስህተት “የሠራው በደል” መጻሕፍት በማንበብ ፣ ከመምህራን ተምሮ ፣ የስብከት ካሴት አዳምጦ ፤ ህሊናው ወቅሶት ፣ ወይም በሌላ በአንድ ምክንያት ስህተት መሆኑን ከተረዳ በኋላ ተፀፅቶ ከእግዚ አብሔር ለመታረቅ (በደሉን ለማስተስረይ) የሚያደርገው ጉዞ ንስሐ ይባላል ። በሠራው በደል ሳይፀፀት ፤ ለጊዜው ህሊናውን ስለረበሸው ብቻ ንስሐ የሚገባ ሰው ፤ ንስሐውን ከጨረሰ በኋላ ወደ ቀደመ ሕይወቱ ሊመለስ ይችላል ። ምክንያቱም ፡ ንስሐ የገ ባው ፡ በሰራው በደል ከልቡ ተፀፅቶ አስቦበት ሳይሆን ፤ በስሜት ተነሳስቶ ነውና ፤ ስሜቱ ሲጠፋ ሥጋዊ ፍላጎቱም ይነሳሳበትና ውሳኔውንም ሊለውጠው ይችላል ።  
2 ኃጢአትን መጥላት ፤ በበደላችን ከተፀፅትን በኋላ የሰራነውን በደል መጥላት አለብን ፤ መጥላት ማለትም ሥራው ትክክል እን ዳልነበረና ወደፊትም መሥራት እንደሌለብን ራሳችንን ማሳመንና ከኃጢዓት መንገድ መራቅ ማለት ነው ።
3 ከንስሐ በኋላ ስላለው ሕይወት መወሰን ፦ አንድ ምዕመን ንስሐ ከመግባቱ በፊት ለወደፊቱ የሚኖረውን ሕይወት አስቀ ድሞ መመርመርና መወሰን ይገባዋል የእግዚአብሔን ቃል ስንሰማ ለጊዜው ልባችን ሊነካ ፣ ምን እናድርግ ልንል እንችላለን ። የሐ ሥ 2 ፥ 37 ። ነገር ግን ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ዓለሙን ወደመምሰል እንደማንመለስ አስቀድመን ራሳችንን መመርመር አለብን ። ብዙዎቹ በስሜት ወደ ክርስትና ከገቡ በኋላ ፤ በጊዜያዊ ነገር ተታለው በድንገት ከሃይማኖት መንገድ ወጥተዋልና ።
በንስሐ ጊዜ
አንድ ምዕመን ካለፈ በደሉ በንስሐ ታጥቦ በአዲስ ሕይወት ራሱን ለማስተካከልና ከእግዚአብሔር ጋር ለመኖር ከወሰነ በኋላ የንስሐ አባት ሊኖረው ይገባል ። ጌታችን “ካህናትን” ራሱን ወክለው መንጋውን እንዲጠብቁ “በምድር ያሰራችሁት በሰማይ የታሰረ በምድር የፈታችሁት በሰማይ የተፈታ ይሁን ” በማለት መንጋውን እንዲጠብቁ ሾሟቸዋልና ። ማቴ 8 ፥ ዮሐ 21 ፥ 15 ። ማቴ 16 ፥ 19 ። አንድ ክርስቲያን በሕይወት ሲኖር ፤ የእግዚአብሔርን መንገድ የሚመራው ፤ ሲሳሳት ንስሐውን ተቀ ብሎ ቀኖና በመስጠት ከእግዚአብሔር የሚያስታርቀው የንስሐ አባት የግድ ሊኖረው ይገባል ። 

ንስሐ የሚገባው ምዕመን በካህኑ ፊት በሚቀርብበት ጊዜ የሚከተሉትን ማሟላት አለበት ።

1 የሠራውን ስህተት በሙሉ ማስታወስ ። ቀኖናው የሚሰጠው እንደ በደሉ ዓይነት ስለሆነ የሠራውን ማስታወስ አለበት ፤ በቃሉ የሚረሳው ከሆነም በጽሁፍ መመዝገብ ያስልጋል ።
2 ሳይቀንሱ (ሳይከፍሉ) በሙሉ መናገር ። “ይህን ብናገር ሰው ምን ይለኛል ?” ብሎ ከባዱን (የሚያሳፍረውን) ነገር መደበቅ የለበትም ። ሲሰራው ያላሳፈረውን ሲናገረው ሊያፍርበት አይገባም ። አንድ ጊዜ ተናግሮ ከህሊናው ካላስወጣው ሁሌም ሲረብ ሸው ይኖራልና ። “እናንተ ሸክማችሁ የከበደ ወደ እኔ ኑ ሸክማችሁን አራግፋለሁ” ተብሏልና በትክክል አስታውሶ መናዘዝና የኃጢአትን ሸክም ማራገፍ ይገባል ። ማቴ 11 ፥ 28 ። ስለ በደላችን በምንናዘዝበት ጊዜ ግን ፤ ከዕገሌ ጋር ፤ በዚህ ጊዜ ፤ በዚህ ቦታ ፤ ይህን አድርጌያለሁ እያልን ፤ ቦታውን ፤ ጊዜውን የሌላ ሰው ስም በዝርዝር እንድንናገር አንገደድም ፣ የሠራነውን በደል ብቻ “ጣዖት አምልኬያለሁ ፤ ሠርቄያለሁ ፤ አመንዝሬያለሁ∙” በማለት በጥቅሉ መናገር እንችላለን ።
3 ኑዛዜ (ራስን መክሰስ)። የንስሐ ዓላማ በራሳችን ድካም የሠራነውን በደል “ዕገሌ አሳስቶኝ∙” እያሉ ሌላውን ሰው ስለ እኛ  ስህተት ተጠያቂ ማድረግ ሳይሆን ፣ አንደበታችንን ከሳሽ ፣ ህሊናችን ምስክር ፣ አድርገን በመጨከን ራሳችንን በእግዚአብሔር ፊት መክሰስ ነው ። አምLካችን የልባችንን መመለስ ፣ አይቶ የሰራነውን በደል ሁሉ እንዳልተሠራ አድርጎ ያነጻናል ። በደልን በንስሐ ይቅር ማለት የእግዚአብሔር የቸርነት ሥራ ነውና ።

ከንስሐ በኋላ

አንድ ምዕመን ንስሐ ከገባ በኋላ  የሚከተሉትን በቅደም ተከተል ማድረግ አለበት ።

1 የተቀበለውን ቀኖና በትክክል መፈጸም ፤ ቀኖና የግሪክ ቃል ሲሆን : መለኪያ ማለት ነው ። ካህኑ ለበደለው ምዕመን እንደ ሃይማኖቱ ጽናት ፣ እንደ አእምሮው ስፋት ፤ የሠራውን በደል መጥኖ ቀኖና ከሰጠው በኋላ እንደታዘዘው መፈጸም አለበት ። የነነዌ ሰዎች ፣ ት. ዮና 3 ፥1 ። ንጉሡ ህዝቅያስ ፣ ኢሳ 38 ፥ 1 ። ቅዱስ ጴጥሮስ ሉቃ 22 ፥ 54 ። እና ሌሎችም ይቅርታን ያገኙት ፤ በበደላቸው ተጸጽተው በማልቀሳቸውና ንስሃ በመግባታቸው ነው ።
በንስሐ ወቅት ፡ መሬት ላይ መተኛት ፣ ምግብ መቀነስ ፣ ከዓለማዊ ነገሮችና ለመንፈሳዊ ሕይወት ከማይመቹ ጓደኞች መራቅ ያስፈልጋል ። በንስሐ ጊዜ እንዳናደርግ ከታዘዝነው ነገር ራሳችንን በመግዛት መቆጠብ አለብን ፤ እግዚአብሔር በቸርነቱ ወደ ድኅነት ከጠራን በኋላ እንደገና ተመልሰን ወደተውነው ድካማችን መመለስ የለብንም ። የጊዜውን ሳይሆን የመጨረሻውን ማሰብ አለብን ። 2 ጢሞ 4 ፥ 10 ። መዝ 6 ፥ 6 ።

2 በደላችን በንስሐ እንደሚሰረይልን ማመን ። ክርስቶስ ደሙን ያፈሰሰው በደላችንን ለመደምሰስ ስለሆነ ከበደላችን ሊያነጻን የታመነ አምላክ ነው ። ከሠራነው ብዙ ኃጢአት አንጻር የሚሰጠን ቀኖና ትንሽ  መስሎ ቢታየንም ። ማሰብ ያለብን የራሳችንን በደል ሳይሆን የእግዚአብሔርን ቸርነት ነው ። ከእኛ በደል የእግዚአብሔር የቸርነት ሥራው እጅግ ይበልጣልና የታዘዝነውን ፈጽመን የቀረውን እንደቸርነትህ ማለት ይገባል ። “የታዘዛችሁትን ባደረጋችሁ ጊዜ የማንጠቅም ባሪያዎች ነን በሉ” ተብለና ልና ። ሉቃ 17 ፥ 10 ።
3 በሥጋውና በደሙ መታተም (መቁረብ) ። አንድ የተራበ ሰው እጁን ስለታጠበ ብቻ አይጠግብም ። የግድ ምግብ መብላት አለበት ። ንስሐ ማለት መታጠብ ፣ ከእድፍ (ከኃጢአት) መንጻት ማለት ሲሆን ፤ ድኅነት የሚገኘው የዘለዓለም ሕይወት የሚ ሰጠውን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን በመቀበል ነው ። ዮሐ 6 ፥ 33 ። ብዙዎቹ መቁረብን እንደ ትርፍ ነገርና በዕድሜ የተገደበ (ለሽማግሌ ብቻ) አድርገው ስለሚቆጥሩት ለመቀበል ሲዘጋጁ አይታዩም ። ነገር ግን ክርስቲያን የሆነ ሁሉ ቅዱስ ቁርባን የግድ ያስፈልገዋል ። ቀኖና የተቀበልንበት በደላችን የሚሰረየው ሥጋውን ስንበላ ፣ ደሙንም ስንጠጣ ነውና ።
4 ሁሌም ለንስሐ መዘጋጀት ። ንስሐ ከገባንና ከቆርብን በኋላ እንደገና በኃጢአት ልንወድቅ እንችላለን ። አምለካችን “ለምን ንስሐ አልገባህም እንጅ ለምን ኃጢአት ሠራህ ? አይልምና” ሁለተኛ ስንበድል ሀፍረት ሳይሰማንና ከኃጢአት መላቀቅ ካልቻልሁ በየጊዜው የንስሐ አባቴን ከማስቸግር አርፌ ብቀመጥ ይሻለኛል በማለት ፡ ሁሉንም እርግፍ አድርገን እንድተወው ፡ ክፉ ሀሳብ በአምሯችን ሊፈታተነን ይችላል ።
ነገር ግን  ከንስሐ በኋላ እንደ መላእክት በቅድስና ብቻ እንኖራለን ማለት ሳይሆን “ ጻድቅ ሰባት ጊዜ ይወድቃል ፤ ሰባት ጊዜ ይነሳል ።” ምሳ 24  ፥ 16 ። እንደተባለ ፡ አምላካችን ብንወድቅ ሊያነሳን ፤ ብንጠፋ ሊፈልገን ፤ ብንርቅ ሊያቀርበን ፤ በኃጢአት ብንረክስ ሊቀድሰን (እንደ ባዘቶ ሊያጠራን) የታመነ አምላክ ስለሆነ ተስፋ ሳንቆርጥ ፤ በኃጢአታችን ሳንደበቅ ፤ ዘወትር ለንስሓ መዘጋጀት አለብን ። ኢሳ 1 ፥ 18 ። 


No comments:

Post a Comment