ጥቅስ

ጌታዬ
እግዚአብሔር ሆይ
እስከዚህ ያደረስኸኝ
እኔ ማን ነኝ ?
ቤቴስ ምንድር ነው?
2 ሳሙ 7፥18

Friday 8 August 2014

ጾመ ፍልሰታ (ጾመ ማርያም)


የፍልሰታ ጾም ከነሐሴ አንድ እስከ አሥራ አምስት ያለው ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን እንደሚተረከው እመቤታችን ያረፈችው በጥር ሃያ አንድ ቀን ነው፡፡ ይህም በሃምሳ ዓ.ም ነው፡፡ ሐዋርያት በድኗን ሊቀብሩ ወደ ጌቴሰማኒ ይዘዋት ሲሄዱ አይሁድ የእመቤታችንን ሥጋ ሊያቃጥሉ ሲመጡ ቅዱሳን መላእክት የእመቤታችንን አስከሬን ወስደው በገነት አኑረውታል፡፡ በስምንተኛው ወር በነሐሴ አስከሬኗን እንደገና ከጌታ ተቀብለው በጸሎትና በምሕላ ቀበሩአት፡፡ በዚህ የቀብር ሥነ-ሥረዓት ላይ ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ ቶማስ አልነበረም፡፡ በተቀበረች በሦስተኛው ቀን እንደ ልጇ ተነስታ ስታርግ ፣ ቶማስ ከሀገረ ስብከቱ በደመና ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ ያገኛታል፡፡ በዚህ ጊዜ ትንሣኤዋን ሌሎች ሐዋርያት አይተው፣ ለእርሱ የቀረበት መስሎት ተናዶ፣ ‹‹...ፈቀደ ይደቅ እምደመናሁ፤ ከደመናው ለመውደቅ ተመኘ›› በፊት የልጅሽን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁ፡፡ አሁን ደግሞ ያንቺን ትንሳኤ ሳላይ ቀረሁ ብሎ ከደመናው ሊወረወር ቃጣው፡፡ በዚህ ጊዜ እመቤታችን ቶማስን አጽናናችው፡፡

አስደናቂው ሞት ፡፡ ድንግል ማርያም የአምላክ እናት ስትሆን ለምን አረፈች ?

 

 
ድንግል ማርያም የአምላክ እናት ስትሆን ለምን አረፈች ?
እግዚአብሔር ዘላለማዊ ኃይሉንና አምላክነቱን ለዓለም ከገለጸበት ታላቅ ሥራ መካከል በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም የገለጸው ድንቅ ሥራው በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛል፡፡ ይህንን ሁኔታ ድንግል ማርያም “ብርቱ የሆነ እርሱ ታላቅ ሥራን በእኔ አድርጓል ስለዚህም ምክንያት ፍጥረት ሁሉ ያመሰግኑኛል” ሉቃ.፩፥፵፱/1፥9/ በማለት ገለጸችው፡፡ ቅድሰት ኤልሳቤጥም የጌታዬ እናት” አለቻት /ሉቃ.፩፥፵፫/1፥43/ “መልአኩ ቅዲስ ገብርኤል ከሴቶች መካከል ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ” /ሉቃ.፩፥፳፰/1፥28/ አላት፡፡ ቅዱስ ዳዊት ልጄ ይላታል መዝ.፵፬፥፱/44፥9/ ሰሎሞን እኅቴ ይላታል /መኃ.፭፥፩/5፥1/ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስም እናት ሆና ተሰጠችው /ዮሐ.፲፱፥፳፮/19፥26/ ይህንን ድንቅ ሥራ ውስንና ደካማ የሆነ አእምሮ ሊገነዘበው ከሚችለው በላይ ነው፡፡
ቅዱስ አግናጢዎስ ዘአንጾኪያ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በጻፈው መልእክቱ እንደገለጸው” የቅድስት ማርያም ዘለዓለማዊ ድንግልና፤ አማኑኤልን መውለዷ፤ የማይሞተው ጌታ ሞት” እነዚህ ሦስቱ ከዚህ ዓለም ጥበበኞችና ገዢዎች የተሰወሩ ምሥጢራት ነበሩ፤ እነዚህ ድንቅ ምሥጢሮች በራሳቸው ከንግግርና ከቋንቋዎች ሁሉ በላይ ሁነው የሚነገሩ በእግዚአብሔር የዝምታ መጎናጸፊያ የተጠቀለሉ ድብቅና ጣፋጭ ምሥጢሮች ናቸው ይላል፡፡