ጥቅስ

ጌታዬ
እግዚአብሔር ሆይ
እስከዚህ ያደረስኸኝ
እኔ ማን ነኝ ?
ቤቴስ ምንድር ነው?
2 ሳሙ 7፥18

Friday 8 August 2014

ጾመ ፍልሰታ (ጾመ ማርያም)


የፍልሰታ ጾም ከነሐሴ አንድ እስከ አሥራ አምስት ያለው ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን እንደሚተረከው እመቤታችን ያረፈችው በጥር ሃያ አንድ ቀን ነው፡፡ ይህም በሃምሳ ዓ.ም ነው፡፡ ሐዋርያት በድኗን ሊቀብሩ ወደ ጌቴሰማኒ ይዘዋት ሲሄዱ አይሁድ የእመቤታችንን ሥጋ ሊያቃጥሉ ሲመጡ ቅዱሳን መላእክት የእመቤታችንን አስከሬን ወስደው በገነት አኑረውታል፡፡ በስምንተኛው ወር በነሐሴ አስከሬኗን እንደገና ከጌታ ተቀብለው በጸሎትና በምሕላ ቀበሩአት፡፡ በዚህ የቀብር ሥነ-ሥረዓት ላይ ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ ቶማስ አልነበረም፡፡ በተቀበረች በሦስተኛው ቀን እንደ ልጇ ተነስታ ስታርግ ፣ ቶማስ ከሀገረ ስብከቱ በደመና ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ ያገኛታል፡፡ በዚህ ጊዜ ትንሣኤዋን ሌሎች ሐዋርያት አይተው፣ ለእርሱ የቀረበት መስሎት ተናዶ፣ ‹‹...ፈቀደ ይደቅ እምደመናሁ፤ ከደመናው ለመውደቅ ተመኘ›› በፊት የልጅሽን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁ፡፡ አሁን ደግሞ ያንቺን ትንሳኤ ሳላይ ቀረሁ ብሎ ከደመናው ሊወረወር ቃጣው፡፡ በዚህ ጊዜ እመቤታችን ቶማስን አጽናናችው፡፡ ከእርሱ በቀር ትንሣኤዋን ሌላ እንዳላየ ነገራው ለምስክር እንዲሆነው ሰበኗን ሰጥታው ዐረገች፡፡ ቶማስ ሐዋርያት ወዳሉበት ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ እመቤታችንን እኮ ቀበርናት ብለው ነገሩት፡፡ እርሱም አውቆ ምስጢሩን ደብቆ ‹‹ሞት በጥር ነሐሴ መቃብር›› አላቸው አንተ ተጠራጣሪ ነህ ሁሌ ብለው መቃብሩን ሊሳዩት ሲከፍቱ አጧት፡፡በዚህ ጊዜ እመቤታችን ተነስታ አርጋለች ብሎ ሁኔታውን ተረከላቸው፤ ለምስክር ይሁንህ ብላ የሰጠቸውንም ሰበኗን አሳያቸው፡፡ ሐዋርያትም ይህን አይተው አመኑ ሰበኗን ቆራርጠው ለበረከት ተከፋፍለው ወደየሃገረ ስብከታቸው ተመልሰዋል፡፡ ይህም ዛሬ ካህናት በእጅ መስቀላቸው ላይ ሚያስሯት መሀረብ ምሳሌ ነው፡፡ በዓመቱ ቶማስ ትንሣኤሽን አይቶ እንዴት እኛ ቅርብን ብለው ከነሐሴ አንድ ጀምረው ሱባኤ ገቡ፡፡ በነሐሴ አሥራ አራት ቀንም ጌታችን እመቤታችንን አምጠቶ እንድትገለጥላቸው አደረገ፤ ቀበሯትም፡፡ በነሐሴ አሥራ ስድስት ቀንም እርገቷን አከበሩ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሀዋርያት ቤተክርስቲያን የእመቤታችንን በረከት ለማግኘት ትጾማለች፡፡ በኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ይህን ጾም በተለይ ሕጻናቱ ያከብሩታል፡፡ በዚህ የአሥራ አምስት ቀን ጊዜ ውስጥ የማይጾምና የማይቆርብ የለም፡፡ ብዙ ምዕመናንም ቤታቸውን እየዘጉ በመቃብር ቤት ሱባዔ ገብተው በጾምና በጸሎት ይሰነብታሉ፡፡
በፍልሰታ ጾም ጊዜ በጠቅላላ በኢትዮጲያ ቤተ ክርስቲያን ያለው ሁኔታ ሕዝቡ፣ ልጅ አዋቂ ሳይል የሚያሳየው ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ ኢትዮጲያ ለእመቤታችን የፍቅር ሃገርዋ መሆኗን ይመሰክራል፡፡ በሌሎች የምስራቅ አሀት አብያተክርስቲያናት ጾሙ ተከበረ ቢሆንም ታሪኩ ግን የእመቤታችን ዕረፍቷም ትንሣኤዋም በነሐሴ ወር ነው ብለው ነው ሚያከብሩት፡፡ እኛ ግን ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን እንዳሳወቁንና እንዳስተማሩን እረፍቷ በጥር ትንሣኤዋ በነሐሴ መሆኑን እናምናን ይህንም እንሰብካለን፡፡ የእግዚአብሔር ቸርነት የወላዲተ አምላክ ቅድስት ድንግል ማርያም በረከትና ምልጃ ከሁላችን ጋር ይሁን ለዘላለሙ አሜን፡፡ ጾሙን ጾመ ደህነት ጾመ በረከት፣ በንሰሀ ተመልሰን ሥጋውና ደሙን ተቀብለን ከእመቤታችን በረከት አግኝተን መንግስቱን ለመወረስ የምንዘጋጅበት ያድርግልን፡፡ አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment