ጥቅስ

ጌታዬ
እግዚአብሔር ሆይ
እስከዚህ ያደረስኸኝ
እኔ ማን ነኝ ?
ቤቴስ ምንድር ነው?
2 ሳሙ 7፥18

Monday 1 September 2014

አባ ሙሴ ጸሊም

    ሰኔ 24 በዚህች ቀን ኢትዮጵያዊው ጻድቅ አባ ሙሴ ጸሊም አረፈ፡፡ አስቀድሞ ሽፍታ፣ ወንበዴ፣ ዘማዊ ፣ጣኦት አምላኪ ነበር፤ በኃላ እንደ አብርሃም አምላኬ ማን ነው? ብሎ ተመራመረ፤ ወደ አስቄጥስ ገዳም ብትሄድ አምላክህ ማን እንደሆነ ይነግሩሃል የሚል ራዕይ አየ፣ ተመለከተ፤ ተነስቶም ሄደ አባ ኤስድሮስን አገኛቸው፤አጽናንተው አረጋግተው ወደ አባ መቃርስ ወሰዱት አባ መቃርስም ንስሃውን ተቀብለው ቀኖና ሰጡት ኋላም አመነኮሱት የሽፍቶች አለቃ የነበረው የመነኮሳት አለቃ እስከመሆን ደረሰ፤ ሰይፉን ወርውሮ ከፍቅር ጋር ተወዳጀ፤ሌሊት እየተነሳ ለሁሉም መነኮሳት ውኃ ይቀዳላቸው ነበር፤ ለሁሉም ይታዘዛቸው ነበር ትንሹም ትልቁም ሙሴ ይህን አድርግሊኝ ይሉታል አርሱም ሁሉንም እሺ ይላል፤ ራሱን ዝቅ አደረገ ትሁትም ሆነ፤ በጸሎቱ ዝናብ ያዘንም ነበር፤ እድሜው መጨረሻ አካባቢ ቡራኬ ሊቀበል ከመነኮሳት ጋር ሆኖ ወደ አባ መቃርስ ሄደ አርሳቸውም ልጆቼ ከእናንተ መካከል በሰማእትነት የሚሞት አለ ብለው ትንቢት ተናገሩ ሙሴ ጸሊምም አባቴ ሰው እኔ ነኝ ሰይፍ የሚያነሱ በሰይፍ ይጠፋሉ የሚል ቃል አለ ይህን ጊዜ በጉጉት ስጠባበቀው ነበር አላቸው፤ እንደተባለውም የበርበር ሰዎች ገዳሙን ሊያጠፉ መጡ መነኮሳቱ ሲሸሹ ሙሴ እዚያው ቀረ ሌሎች ሰባት መነኮሳት ከአባታችን ጋር እንሞታለን ብለው አብረውት ሆኑ የበርበር ሰዎች ደረሱ ሁሉንም በሰይፍ ገደሏቸው፤ ይህም ሰኔ 24 ቀን ነው፤ የአባታችን የሙሴ ጸሊም ስጋው በገዳመ አስቄጥስ በክብር ይገኛል፤ ግብጻውን ቤተ ክርስቲያን ሰርተውለት ታቦት ቀርጸውለት በየዓመቱ በድምቀት ያከብሩታል ገድሉን ጽፈውለታል ፊልምም ሰርተውለታል ይህን ፊልም የኛ ሰዎች ግሩም አድርገው ወደ አማርኛ መልሰውታል፤ የዛሬዋን ቀን ስለ ተክለ ሃይማኖት ብቻ ብለን አንመጽውት ስለ አባ ሙሴ ጸሊምም እያልን ይሁን እንጂ፤ አምላከ ተከልዬ ጠብቀኝ ስንል አምላከ ሙሴ ጸሊም አትርሳኝ ማለትንም አንርሳ የዚህ ድንቅ አባት ታሪክ የማይረሳ ነውና፡፡
 ሙሴ ጸሊም ማለት ጥቁሩ ሙሴ ማለት ነው፤ መልኩ ጥቁር ስለሆነ ነው ጥቁሩ ሙሴ ተብሎ የተጠራው፤ በነገራችን ላይ ከዕለታት በአንዱ ቀን በዚሁ በጥቁረቱ የተነሳ አባቶች አንድ ፈተና አቅርበውለት ነበር፣ አባ ኤስድሮስ ይጠሩትና ሙሴ ዛሬ ቀድሰክ ታቆርባለህ ይሉታል እርሱም እሺ አባቴ ብሎ ይወጣል በዚህን ጊዜ አባ እስድሮስ ካህናቶችን ይጠሩና ዛሬ ሙሴ ቅዳሴ ሊቀድስ ወደ መቅደስ ሲገባ ሰድባችሁ አባሩት ብለው ትዕዛዝ ይሰጣሉ እንደተባለው ሙሴ ሊቀድስ ልብሰ ተክህኖ ለብሶ ወደ መቅደስ ሊገባ ሲል አንተ ጥቁር ብለክ ብለክ ከኛ ጋር መቀደስ አማረክ ወግድ ከዚህ ብለው ያባርሩታል እርሱም ምንም ሳይናገር አንገቱን አቀርቅሮ ትክክል ናቸው ያለ ቦታክ ለምን ገባክ እያለ እራሱን እየወቀሰ ተመለሰ የሚገርመው ቂም ሳይዝባቸው በነጋታው ውኃ ሊቀዳላቸው ሄደ ይህን የተመለከቱ አባ እስድሮስ ጠርተው ሙሴ ያቀረብንልክን ፈተና አልፈካል እግዚአብሔር ካንተ ጋር ይሁን ብለው መርቀውታል። መጽሐፈ መነኮሳት 2ኛው ከአባ ሙሴ ጸሊም ከጻድቁ ተክልዬ በረከት ያሳትፈን።

No comments:

Post a Comment