ጥቅስ

ጌታዬ
እግዚአብሔር ሆይ
እስከዚህ ያደረስኸኝ
እኔ ማን ነኝ ?
ቤቴስ ምንድር ነው?
2 ሳሙ 7፥18

Saturday 6 September 2014

ፈታሄ ማህጸን ቅዱስ ሩፋኤል

በታናሹ ወር በ 3ኛው ቀን በዓሉን አድርጉለት ይኸውም ጳጉሜን ነው ።
ጳጉሜን 3 የመላአክት አለቃ የከበረ መልአክ የሩፋኤል መታሰቢያ ነው ።
ይኸውም ትጉሃን ቅዱሳን ሰማያውያን ከሚሆኑ ከመላአክት አለቆች ከቅዱስ ሚካኤልና ከቅዱስ ገብርኤል ቀጥሎ 3ተኛ ነው ። ፈታሄ ማህጸን ቅዱስ ሩፋኤል እግዚአብሔር በ23ቱ ነገደ መላእክት ላይ ሾሞታል፡፡
በዚያች በድህነትና በደስታ ቀን ለሕዝበ ክርስቲያን ከዕፀ ህይወት ይሰጣቸዉ ዘንድ እግዚአብሔር ያዘዘዉ ቅዱስ ሩፋኤልን ነዉ ።
...
ሰማያዉያን መዛግብት በእጁ የሚጠብቃቸው እግዚአብሔር እንዳዘዘዉ የሚከፍታቸዉ የሚዘረጋቸዉ ይህ ታላቅ መልአክ ነዉ፡፡
በዚህ ዕለት ተዝካሩ መደረጉ ስለ 2 ነገር ነው የመጀመሪያው በዓለ ሢመቱ ስለሆነ ነው ።
ዳግመኛም የእስክንድርያው ሊቀጳጳሳት አባ ቴዎፍሎስ መሬት ውስጥ 3 ድስት ሙሉ ወርቅ አግኝቶ በአንዱ በድስት ሙሉ ወርቅ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት አሰርቷል ። ከእነዱም አንዲቱ ከእስክንድርያ ውጭ በአለች ደሴት ላይ በቅዱስ ሩፋኤል ስም ቤተክርስትያን አሰርቶ ስራዋን ጨርሶ እንደዛሬይቱ በአለች ቀን ቀደሳት ።
ምእመናት ከቤተክርስትያን ውስጥ እየፀለዩ ሳሉ እንሆ ቤተክርስቲያኒቱ ተንቀጠቀጠች ተናወጠች ታወከች ።
በመረመሩም ጊዜ ከባህር አንባሪዎች በአንዱ ታላቅ ዓሣ አንባሪ ላይ ተሰርታ አገኙዋት ። ዓሣ አንባሪውም ከቦታው ሳይንቀሳቀስ ኑሮ ነበር ።
በላዩ የሰው ሁሉ እግር በበዛና በከበደው ጊዜ ቤተክርስቲያኒቱን ያፈርሳት ዘንድ ሰይጣን አወከው። ምእመናትና ጳጳሱ ወደ እግዚአብሔር ቢያመለክቱ ቅዱስ ሩፋኤል ተልኮ ፡ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ጸንትህ ቀም ከቦታህም አትንቀሳቀስ ብሎ ዓሣውን በጦር ወጋው ። ያን ጊዜም ዓሣ አንባሪው በቦታው ጸንቶ ቆመ አልተንቀሳቀሰም ።
በዚችም ቤተክርስትያን ብዙ ውስጥ ብዙ ድንቅ ተአምራት ተደረገ ። " በሰዉ ቁስል የተሾመ ፤በፈዉስ ላይ የተሾመ፤ ከከበሩ መላእክት አንዱ ቅዱስ ሩፋኤል ነዉ፡፡ሄኖክ 6፡3 " እንዲል ለታመሙትም ታላቅ ድኅነት ሆነ ።
የዋህ የምህረትና የረድኤት መልአክ ቅዱስ ሩፋኤል ከስራዎቹ አንፃር በተለያየ ስም ይጠራል ለአብነት ያክል ፡-
=> "ፈታሄ ማህጸን" ይባላል ። እናቶች ሲወልዱ ምጥ እንዳይበዛባቸዉ የሚራዳ መልአክ ስለሆነ አያሌ ክርስቲያኖች ማርገዛቸዉን ካወቁ ጀምሮ ድርሳኑን በማንበብ መልኩን በመድገም ጠበሉን በመጠጣት ሰዉነታቸዉን በመቀባት ይለምኑታል፡፡እንደ እምነታቸዉ ጽናት ይደረገላቸዋል፡፡
=> "ዐቃቤ ኖኀቱ ለአምላክ" ይባላል፡፡ ሰማያዉያን መዛግብት በእጁ የሚጠበቅ በመሆኑ ።
=> "መራሔ ፍኖት" ይባላል፡፡ ጦቢትን በቀና መንገድ መርቶታልና፡፡
=> "መላከ ክብካብ" ይባላል ። ጦቢያና ሣራን ያጋባ ጋብቻቸዉን የባረከ በመሆኑ፡፡

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን የከበረ የመላእክት አለቃ የሩፋኤል ይቅርታ ልመናውና በረከቱ ከእኛ ጋር ይኑር ለዘለዓለሙ አሜን ።

No comments:

Post a Comment