- ታላቁ መቃርስ ከመልካምና ቅዱሳን ቤተሰብ ሻብሺር መኑፍ በተባለ አከባቢ ተወለደ። አባቱ አብራግ እናቱ ደግሞ ሳራ ይባላሉ። ወንድ ልጅ አልነበራቸውም። አብራግ በሕልሙ የእግዚአሔር መልአክ መጥቶ ወንድ ልጅ ትወልዳላችሁ ስሙም በምድር ሁሉ የታወቀ እንደሚሆንና ብዙ ደቀ መዛሙርን እንደሚያፈራ ገለጸለት።
ሕጻኑ ሲወለድ ገና መቃርስ አሉት ...ትጉሙም የተባረከ ማለት ነው።
ሰይጣን በአንድ ወቅት ለአባ መቃርስ ጠላቶችህ በጣም በዙ ሲለው አባ መቃርስ “ሰው የሰው ጠላት የለውም” አለውና ሰይጣንን አሳፈረው! ዲያቢሎስም ታዲያ የሰው ጠላት ማን ነው? ብሎ አባ መቃርስን ጠየቀው። አባ መቃርስም የሰው ጠላትማ የእለተ አርቡን ሰው አዳምን የፈተነ ፣ ኢዮብን ፣ ዳዊትን ፣ የበቁ አባቶችን በሙሉ የፈተነ አንድ ፍጥረት ነበር፤ ጠላት እሱ ነው! “አንተ ይህን ፍጥረት አታውቀውም እንዴ?” አለው። ዲያቢሎስም ኧረ በጭራሽ ሰምቼ አላውቅም አንዳችም የማውቀው ነገር የለኝም፤ ይገርማል! እንዴት ያለ ጨካኝ ነው አለ ራሱን እየነቀነቀ! አባ መቃርስም አዎ እንዳልከው ጨካኝ ነው፤ ይህን ፍጥረት አለማወቅህ ግን ገርሞኛል። ይገርምሃል እሱ ጨካኝ ብቻ ሳይሆን የፈጠረውን በገዳመ ቆሮንጦስ የፈተነ ደፋርም ጭምር ነው። ጨካኝና ደፋር ቢሆንም በጌታችን ድል ተነስቷልና እኛም ይህችን ጾም ሰሞኑን እየጾምን እኮ ነው አለው። ይህን ግዜ “ዲያቢሎስ ድል ተነስቷል” የሚለውን ቃል ሲሰማ ሽንፈቱ ትዝ አለውና ተቁነጠነጠ።እንዳይታወቅበት ግን “አይ ደፋሩ ጉድ ጉድ! እያለ ማስመሰሉን ቀጠለ። አባ መርቃስም እንዴ አንተ ይህን ካላወቅህ አትጾምም ማለት ነው እንዴ? አለው ፈገግ እያለ። ዲያቢሎስም ጾ… ጾ ….. ም…. ጾም ትንሽ ስለሚያመኝ…. እያለ ሲቀባጥር አባ መርቃስ አሁንም ፈገግ እያለ አይ አንተ የሰው ጠላት የምትሆነው እስከ መቼ ነው? መታመሜን አውቀህ እንዳልጾም ይህን ሁሉ ቀባጠርክ። ገና ስትመጣ ማን እንደሆንክ አውቅ ነበር! ገና እኔን ለመፈተን ስታስብ አውቅ ነበር! አይ ዲያቢሎስ የሰው ጠላት አንተ ብቻ ነህ! በል አሁን የጾም ግዜ ነውና ዞር በል ብሎ ገሰፀው። ዲያቢሎስም ከእርሱ ራቀ። ይህን የአባ መቃርስን ታሪክ ሳነብ አንድ ነገር ትዝ አለኝ፤ “ዲያቢሎስ እንደ ሚያገሳ አንበሳ በዙሪያችሁ ይዞራል በእምነት ሆናችሁ ተቃወሙት ከእናንተም ይሸሻል” የምትለዋ የሐዋርያው መልዕክት ፩ኛ ጴጥሮስ [፭:፰] ይህን በደንብ እንረዳ ሰው የሰው ጠላት የለውም፤ ጠላት ማን ነው? ጠላት ዲያቢሎስ ነው።
ጥቅስ
ጌታዬ
እግዚአብሔር ሆይ
እስከዚህ ያደረስኸኝ
እኔ ማን ነኝ ?
ቤቴስ ምንድር ነው?
2 ሳሙ 7፥18
እግዚአብሔር ሆይ
እስከዚህ ያደረስኸኝ
እኔ ማን ነኝ ?
ቤቴስ ምንድር ነው?
2 ሳሙ 7፥18
Wednesday, 25 December 2013
Friday, 6 December 2013
ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
- ♥በስመ ሥላሴ♥
“ሳጥናኤል ይማር አለም ይዳን”
==> ኢትዮጵያዊት ጻድቅ የእምነት ሴት አርበኛ ጻድቅ ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ <==
ጌታም ይህን ሁሉ መከራ እንደ መስዋዕት ቆጥሮላት አእላፍ መላእክቱን አስከትሎ መጥቶ በተስፋዋ ያመነውን ቃል ኪዳኗ የተማጸነውን እስከ 10 ትውልድ ድረስ እንዲምርላት ተስፋዋን ነግሯታል።
==> “የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደ ጻድቃን ጆሮቹም ወደ ጩ...ኸታቸው ናቸውና …. ጻድቃን ጮኹ፥ እግዚአብሔርም ሰማቸው ከመከራቸውም ሁሉ አዳናቸው……የጻድቃን መከራቸው ብዙ ነው፥ እግዚአብሔርም ከሁሉ ያድናቸዋል…ጻድቃንንም የሚጠሉ ይጸጸታሉ። <== ” መዝ.፴፫፥፲፯¬-፳፩ (33፥17¬-21
==> ሀገሯ ቡለጋ ቅድስጌ ልዩ ስሙ ጥጥ ምድር አከባቢ ነው። አባቷ ቅዱስ ደረሳኒ እናቷ ቅድስት እሌኒ ይባላሉ። ቤተሰቦች በክብር በስርዓት ቅድሳት መጽሐፍትን ብሉይ ከሐዲሳት እያስተማሩ ባደገችና ለአካለ መጠን (ለአቅመ ሔዋን) ስትደርስ የመኳንንት የመሳፍንት ልጅ ናትና ለንጉስ ባለሟል ለሆኑ ትውልድ ነገዱ ፃሰርጓ ወገን ሲሆን የኢሱስ ሞዓ ልጅ ሠምራ ጊዮርጊስ ለሚባል ደግ ካህን በሕግ በ14 ዓመቷ ዳሯት። ፲፪ ልጆችም ወልዳለች።
==> ከመከራዋ ብዛት ከገድሏ ጽናት ሰውነቷ ተበሳስቶ የዓሣ መመላለሻ እስኪሆን ድረስ ከባህሩ ገብታ ወደ ግራና ቀኝ ሳትል ፲፪ ዓመት ጸለየች። በመጨረሻም ጌታ ምን አደርግልሽ ትሽያለሽ?
Sunday, 3 November 2013
ምሥጢረ ንስሐ
ምሥጢረ ንስሐ
ንስሐ ፦ ነስሐ ተፀፀተ ካለው የተገኘ ሲሆን ፤ ንስሐ ማለት በሠሩት ኃጢአት መፀፀት ፣ ማዘን ፣ ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ መወሰን ፤ ማለት ነው ። ንስሐ ከዘለዓለማዊ ፍርድ የሚያድን ፤ ዘማዊውን እንደ ድንግል ፤ ሌባውን መጽዋች የሚያደርግ በፊት ከተሠራው ኃጢአት ንጹህ አድርጎ ፤ ከእግዚአብሔር ጋር አንድ የሚያደርግ ምሥጢር ነው ።
ንስሐ ፦ ከንስሐ በፊት ፣ በንስሐ ጊዜ ፣ ከንስሐ በኋላ፤ ተብሎ በሶስት ይከፈላል
ከንስሐ በፊት
1 መፀፀት ፤ አንድ ክርስቲያን በድፍረትም ይሁን በስህተት “የሠራው በደል” መጻሕፍት በማንበብ ፣ ከመምህራን ተምሮ ፣ የስብከት ካሴት አዳምጦ ፤ ህሊናው ወቅሶት ፣ ወይም በሌላ በአንድ ምክንያት ስህተት መሆኑን ከተረዳ በኋላ ተፀፅቶ ከእግዚ አብሔር ለመታረቅ (በደሉን ለማስተስረይ) የሚያደርገው ጉዞ ንስሐ ይባላል ። በሠራው በደል ሳይፀፀት ፤ ለጊዜው ህሊናውን ስለረበሸው ብቻ ንስሐ የሚገባ ሰው ፤ ንስሐውን ከጨረሰ በኋላ ወደ ቀደመ ሕይወቱ ሊመለስ ይችላል ። ምክንያቱም ፡ ንስሐ የገ ባው ፡ በሰራው በደል ከልቡ ተፀፅቶ አስቦበት ሳይሆን ፤ በስሜት ተነሳስቶ ነውና ፤ ስሜቱ ሲጠፋ ሥጋዊ ፍላጎቱም ይነሳሳበትና ውሳኔውንም ሊለውጠው ይችላል ።
Sunday, 29 September 2013
አቡነ አኖሬዎስ ዘደብረ ጽጋጋ
| አቡነ አኖሬዎስ ዘደብረ ጽጋጋ |
መስከረም 13 ቀን 2005 ዓ.ም.
በመ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ ለአቡነ አኖሬዎስ ወላጆቻቸው ያወጡላቸው ስም ናርዶስ ሲሆን በሕፃንነታቸው የዳዊትን ንባብና የመጻሕፍትን ትርጓሜ ከተማሩ በኋላ በወቅቱ ከነበሩበት ግብፃዊ ጳጳስ ዲቁና ተቀበሉ፡፡ በወቅቱ ሐራንኪስ የተባለ የትርጓሜ መጻሕፍትና የዜማ ዐዋቂ በቤታቸው በእንግድነት ለብዙ ጊዜ በቆየበት ወቅት ለአቡነ አኖሬዎስ ዜማና ትርጓሜ መጻሕፍት በሚገባ አስተምሯቸዋል፡፡ በዚህም ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን፣ ዜማና ትርጓሜ መጻሕፍት የበለጠ ለመረዳት ከነበራቸው ፍላጎት አንጻር ወደ ደብረ አስቦ (ደብረሊባኖስ) በመሔድ ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት ጋር ተገናኙ፡፡ በደብረ አስቦ (ደብረሊባኖስ) በገዳም ለረዥም ዓመታት ካገለገሉና ከተማሩ በኋላ በአቡነ ተክለ ሃይማኖት እጅ መንኩሰው አባ አኖሬዎስ ተባሉ፡፡ የገዳሙ መነኮሳት በሊቀ ዲያቆንነት መርጠዋቸው ትርጓሜ መጻሕፍትና ዜማ ያስተምሯቸው ነበር፡፡ ትጋታቸውን ያዩት የገዳሙ መነኮሳትም ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት በታች የገዳሙ መጋቢ አድረገው መረጧቸው፡፡ በዚያ ዘመን በገዳሙ ወንዶች እና ሴቶች መነኮሳዪያት በአንድነት ይኖሩ ነበር፡፡ ነገር ግን አቡነ አኖሬዎስ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን አማክረው የሴትና የወንድ ገዳም እንዲለይ አደረጉ፡፡ ከዚህ በኋላ በወቅቱ በነበሩት አቡነ ቄርሎስ ዘንድ ተልከው ቅስናን ተቀበሉ፡፡ |
Wednesday, 31 July 2013
ትምህርተ ጋብቻ ክፍል ፫ (3)
ከ መልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው ብሎግ የተወሰደ
፩፦ መጠናናት፤
ምንም እንኳን የሰው ልጅ ተጠንቶ የማያልቅ ሳይንስ ቢሆንም ፦ ወደ ትዳር ዓለም ከመግባት በፊት ፦እንደ ሰው፥ በሰው አቅም መጠናናት እንደሚያስፈልግ ለማንም ግልጥ ነው። ይኸውም በሰከነ ልቡና ፥ በተረጋጋ መንፈስ ሊሆን ይገባል። በትውውቅ ሰሞን የተሸፈነ ብዙ ነገር ፥ በሂደት ቀስ እያለ ብቅ ማለቱ ስለማይቀር ጊዜ መስጠት ያስፈልጋል። ሰውን የምናጠናው ድካም የሌለበት ፍጹም የሆነ ሰው ለማግኘት አይደለም። ምክንያቱም እኛም ፍጹም አይደለንምና ነው ፥ አንድም በዓለመ ሥጋ ፍጹም ሰው አይገኝምና ነው። በመሆኑም፦ በእኛ ዘንድ ድካም እንዳለ ሁሉ ፦ በሌላም በኲል ድካም ሊኖር እንደሚችል አምነን ኅሊናችንን ልናዘጋጀው ይገባል። ከዚ ህ በኋላ ድካሙን ፦ በአራት ደረጃ ከፍለን ልናየው እንችላለን። ፩ኛ፦ በቶሎ የሚወገድ ድካም ፤ ፪ኛ ፦ በሂደት የሚወገድ ድካም፤ ፫ኛ፦ ልንሸከመው የሚገባን ድካም፤ ፬ኛ ፦ የማይወገድ ድካም፤
፩፥፩፦ በቶሎ የሚወገድ ድካም፤
የሰው ልጅ በትምህርት ፥ በምክርና በተግሣጽ ፦ ከጥፋቱ ሊመለስ ፥ ከድካሙም ሊበረታ ይችላል። ስለሆነም ያሉትን ደካማ ጐኖች ዘርዝሮ በማውጣት ፦ እርስ በርስ መነጋገር ፥ መማማር ያስፈልጋል። ከአቅም በላይ የሆነውን ደግሞ ወደ ካህኑ በማምጣት ማስ መከር ይገባል። እንዲህ ዓይነቱ ድካም ፦ ከእውቀት ማነስ፥ ከመካሪ ማጣት ፥ አርአያ የሚሆን ሰው ካለማግኘት በመሆኑ በቶሎ ይወ ገዳል። ጠቢቡ ሰሎሞን፦ «ምክር በሰው ልቡና እንደ ጥልቅ ውኃ ነው፤ አእምሮ ያለው ሰው ግን ይቀዳዋል።» እንዳለ፦ አእምሮ ያላቸው የሚያስተውሉ ሰዎች ይስተካከሉበታል። ምሳ ፳፥፭። «ተግሣጽን የሚወድድ ዕውቀትን ይወድዳል፤» እንዲል፦ በሁሉ ይገሠጻሉ። ምሳ ፲፪፥፩። «የተማረ ልጅ ብልህ ይሆናል፤» እንዲል፦ ልባሞች ፥ አስተዋዮች እየሆኑ ይሄዳሉ። ምሳ ፲፥፭። ይህም ከምድራዊ ሀብት የሚበልጥ ሀብት ነው። ምክንያቱም « ከብር ይልቅ ትምህርትን ፥ ከተፈተነ ወርቅም ይልቅ ዕውቀትን ተቀበሉ ፤ » ይላልና። ምሳ ፰፥፲። «ትምህርትና ተግሣጽም የሕይወት መንገድ ነውና፤» የሚልም አለ። ምሳ ፮፥፳፫።
ትምህርተ ጋብቻ፡- ክፍል ፪ (2)
ከ መልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው ብሎግ የተወሰደ
፩፡- የትዳር ጓደኛን ማን ይምረጥልን?
የሰው ልጅ በእምነቱም ሆነ በሌላው ነገር ሁሉ ፍጹምነት ስለሌለው በፍለጋው (በመንገዱ) አጋዥ ያስፈልገዋል። ያንንም የሚሰጠን ያለ ጥርጥር እግዚአብሔር ነው። ለዚሀም የጾምና የጸሎት ሰው መሆን ያስፈልጋል። የነቢያት አለቃ ሙሴ ጽላቱን ከእግዚአብሰሔር እጅ የተቀበለው አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት ጾሞ ነው፥ እንጀራ አልበላም፥ ውኃም አልጠጣም። ዘጸ ፴፩፥፲፰። እኛም እንደ ጽላት እንደ ታቦት ተከብረው የሚያስከብሩ የትዳር ጓደኞቻችንን በጾምና በጸሎት ልናገኛቸው እንችላለን ብለን ልናምን ይገባል። በአገራችን፡-«አቶ እገሌ እኮ ታቦት ማለት ናቸው፥ ወ/ሮ እገሊት እኮ ታቦት ማለት ናቸው፤» የሚባሉ ነበሩ። ታቦት የሚያሰኛቸው የጸና ሃይማኖታቸው፥ የቀና ምግባራቸው ነበረ።
ትምህርተ ጋብቻ ክፍል ፦ ፩
ከ መልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው ብሎግ የተወሰደ
http://www.betedejene.org/2010/12/blog-post.html
http://www.betedejene.org/2010/12/blog-post.html
፩፦ « መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር ነው፤» ዕብ ፲፫፥፬
ጋብቻን ባርኮና ቀድሶ ለሰው ልጅ የሰጠው እግዚአብሔር ነው። በመሆኑም ጋብቻ የእግዚአብሔር ጸጋ ነው። ስለዚህ በዓይን ምኞት ተጋርደው፥ በሥጋ ፍላጐት ተነድተው ፥ በስሜት ፈረስ ጋልበው ፥ የሚገቡበት ሳይሆን ፦ በጸሎት እና በምልጃ ፈቃደ እግዚአብሔርን ጠይቀው የሚፈጽሙት ታላቅ ምሥጢር ነው።
ጋብቻ የሰው ሁሉ ሕልም ነው። የማይመኘው፥የማይፈልገው የለም። የሰው ሁሉ ጸሎት፥ የሰው ሁሉ ስእለት ነው። ለመሆኑ፦ ህልሙ የተፈታለት ፥ ጸሎቱ የደረሰለት ፥ ስዕለቱ የሰመረለት ስንቱ ይሆን? ያላገባው ይናፍቃል ፥ ያገባው ደግሞ ያማርራል። ከጋብቻ በፊት « መልአክ » የተባለ የትዳር ጓደኛ ከጋብቻ በኋላ «ሰይጣን» ይባላል። «እኔ የመረጥኩትን ካላገባሁ እሰቀላለሁ፤» እንዳልተባለ «ካልተፋታሁ መርዝ እጠጣለሁ፤» ለማለት ችግር የለም። ከጋብቻ በፊት ምክር ላለመስማት አሳብ ላለመቀበል፦ «ስለ እኔ ማንም አያገባውም፤» ተብሎ በር እንዳልተዘጋ ሁሉ ከጋብቻ በኋላ ግን ጣልቃ የማያስገቡት ሰው የለም ፤ «ምን በወጣህ ፥ ምን በወጣሽ፤» የሚለውን ፈጥኖ ለመቀበል በሩ ለሁሉም ክፍት ነው።
፪፦ ጋብቻ እንዴት ተጀመረ?
ጋብቻ በአዳምና በሔዋን እንደተጀመረ የጎላ፥ የተረዳ ፥ የታወቀ ነገር ነው። «ተባዕተ ወአንስተ ገብሮሙ፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው፤ » እንዲል፦ አዳም ሲፈጠር ሔዋን በውስጡ ነበረች። ዘፍ ፩፥፳፰። ይህም በባህርዩ ነበረች ማለት ነው። አንድ አካል፥ አንድ ሥጋ ከሚያሰኛቸው ምሥጢር አንዱና ዋነኛውም ይኸው ነው።
ጋብቻ የተጀመረው በአዳም ጥያቄ ነው፤ ጥያቄዎም የኅሊና ማለትም ውሳጣዊ ነበር። ምክንያቱም፦ ከላይ እንደተ መለከትነው፦ የትዳር ጓደኛው በውስጡ ስለነበረች ነው። « እግዚአብሔር አምላክም፦ ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም፤ የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት፥አለ፤»ይላል። እግዚአብሔር እንዲህ ማለቱ፦ በአዳም ኅሊና ውስጥ ይህ ጥያቄ እንደሚነሣ ስለሚያውቅ ነው። መናገሩም ለአዳም ኅሊና እንጂ ፥ ሔዋን ለአዳም እንደምትፈጠርለት አስቀድሞ በእግዚአብ ሔር ዘንድ የተወሰነ ነው።
Subscribe to:
Posts (Atom)



