ጥቅስ

ጌታዬ
እግዚአብሔር ሆይ
እስከዚህ ያደረስኸኝ
እኔ ማን ነኝ ?
ቤቴስ ምንድር ነው?
2 ሳሙ 7፥18

Saturday 20 December 2014

መልአኩን ልኮ አዳናቸው

በስመአብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
                  በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ታህሣሥ 19 ከከበሩት መላእክት አንዱ የሆነው የቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ ክበረ በዓል በታላቅ መንፈሳዊ ድምቀት በመዝሙር በጸሎት በምስጋና በቅዳሴ በዝክር ይከበራል ይታሰባል። የሚከበርበት ምክንያት ብርሃናዊ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ሠለሥቱ ደቁቅን ከዕቶነ እሳት(ከነደደ እሳት) ያዳነበት ዕለት በመሆኑ ነው፡፡
          ቅዱስ ገብርኤል ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃ ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱና በእግዚአብሔር ፊት የሚቆመው ታማኝ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ነው ብሏል ሉቃ 1፥20 
ታላቁ ነብይ ሄኖክ ስለ ነገረ መላእክት በተናገረበት አንቀጽ እንዲህ ሲል መሰክሯል << በባቦች ላይ በገነትም በጸድቃን ላይ በኪሩቤልም ላይ የተሾሙ ከከበሩ መላእክት አንዱ ገብርኤል ነው ፡፡>> ሄኖክ 6-7<< በሦስተኛውም  በመላእክት ሁሉ ላይ የተሾመ  ቅዱስ  ገብርኤል ነው >>1014 እያለ የመልአኩን ክብር ተናግሯል

Saturday 6 September 2014

ፈታሄ ማህጸን ቅዱስ ሩፋኤል

በታናሹ ወር በ 3ኛው ቀን በዓሉን አድርጉለት ይኸውም ጳጉሜን ነው ።
ጳጉሜን 3 የመላአክት አለቃ የከበረ መልአክ የሩፋኤል መታሰቢያ ነው ።
ይኸውም ትጉሃን ቅዱሳን ሰማያውያን ከሚሆኑ ከመላአክት አለቆች ከቅዱስ ሚካኤልና ከቅዱስ ገብርኤል ቀጥሎ 3ተኛ ነው ። ፈታሄ ማህጸን ቅዱስ ሩፋኤል እግዚአብሔር በ23ቱ ነገደ መላእክት ላይ ሾሞታል፡፡
በዚያች በድህነትና በደስታ ቀን ለሕዝበ ክርስቲያን ከዕፀ ህይወት ይሰጣቸዉ ዘንድ እግዚአብሔር ያዘዘዉ ቅዱስ ሩፋኤልን ነዉ ።
...
ሰማያዉያን መዛግብት በእጁ የሚጠብቃቸው እግዚአብሔር እንዳዘዘዉ የሚከፍታቸዉ የሚዘረጋቸዉ ይህ ታላቅ መልአክ ነዉ፡፡
በዚህ ዕለት ተዝካሩ መደረጉ ስለ 2 ነገር ነው የመጀመሪያው በዓለ ሢመቱ ስለሆነ ነው ።
ዳግመኛም የእስክንድርያው ሊቀጳጳሳት አባ ቴዎፍሎስ መሬት ውስጥ 3 ድስት ሙሉ ወርቅ አግኝቶ በአንዱ በድስት ሙሉ ወርቅ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት አሰርቷል ። ከእነዱም አንዲቱ ከእስክንድርያ ውጭ በአለች ደሴት ላይ በቅዱስ ሩፋኤል ስም ቤተክርስትያን አሰርቶ ስራዋን ጨርሶ እንደዛሬይቱ በአለች ቀን ቀደሳት ።
ምእመናት ከቤተክርስትያን ውስጥ እየፀለዩ ሳሉ እንሆ ቤተክርስቲያኒቱ ተንቀጠቀጠች ተናወጠች ታወከች ።

Monday 1 September 2014

አባ ሙሴ ጸሊም

    ሰኔ 24 በዚህች ቀን ኢትዮጵያዊው ጻድቅ አባ ሙሴ ጸሊም አረፈ፡፡ አስቀድሞ ሽፍታ፣ ወንበዴ፣ ዘማዊ ፣ጣኦት አምላኪ ነበር፤ በኃላ እንደ አብርሃም አምላኬ ማን ነው? ብሎ ተመራመረ፤ ወደ አስቄጥስ ገዳም ብትሄድ አምላክህ ማን እንደሆነ ይነግሩሃል የሚል ራዕይ አየ፣ ተመለከተ፤ ተነስቶም ሄደ አባ ኤስድሮስን አገኛቸው፤አጽናንተው አረጋግተው ወደ አባ መቃርስ ወሰዱት አባ መቃርስም ንስሃውን ተቀብለው ቀኖና ሰጡት ኋላም አመነኮሱት የሽፍቶች አለቃ የነበረው የመነኮሳት አለቃ እስከመሆን ደረሰ፤ ሰይፉን ወርውሮ ከፍቅር ጋር ተወዳጀ፤ሌሊት እየተነሳ ለሁሉም መነኮሳት ውኃ ይቀዳላቸው ነበር፤ ለሁሉም ይታዘዛቸው ነበር ትንሹም ትልቁም ሙሴ ይህን አድርግሊኝ ይሉታል አርሱም ሁሉንም እሺ ይላል፤ ራሱን ዝቅ አደረገ ትሁትም ሆነ፤ በጸሎቱ ዝናብ ያዘንም ነበር፤ እድሜው መጨረሻ አካባቢ ቡራኬ ሊቀበል ከመነኮሳት ጋር ሆኖ ወደ አባ መቃርስ ሄደ አርሳቸውም ልጆቼ ከእናንተ መካከል በሰማእትነት የሚሞት አለ ብለው ትንቢት ተናገሩ ሙሴ ጸሊምም አባቴ ሰው እኔ ነኝ ሰይፍ የሚያነሱ በሰይፍ ይጠፋሉ የሚል ቃል አለ ይህን ጊዜ በጉጉት ስጠባበቀው ነበር አላቸው፤ እንደተባለውም የበርበር ሰዎች ገዳሙን ሊያጠፉ መጡ መነኮሳቱ ሲሸሹ ሙሴ እዚያው ቀረ ሌሎች ሰባት መነኮሳት ከአባታችን ጋር እንሞታለን ብለው አብረውት ሆኑ የበርበር ሰዎች ደረሱ ሁሉንም በሰይፍ ገደሏቸው፤ ይህም ሰኔ 24 ቀን ነው፤ የአባታችን የሙሴ ጸሊም ስጋው በገዳመ አስቄጥስ በክብር ይገኛል፤ ግብጻውን ቤተ ክርስቲያን ሰርተውለት ታቦት ቀርጸውለት

Friday 8 August 2014

ጾመ ፍልሰታ (ጾመ ማርያም)


የፍልሰታ ጾም ከነሐሴ አንድ እስከ አሥራ አምስት ያለው ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን እንደሚተረከው እመቤታችን ያረፈችው በጥር ሃያ አንድ ቀን ነው፡፡ ይህም በሃምሳ ዓ.ም ነው፡፡ ሐዋርያት በድኗን ሊቀብሩ ወደ ጌቴሰማኒ ይዘዋት ሲሄዱ አይሁድ የእመቤታችንን ሥጋ ሊያቃጥሉ ሲመጡ ቅዱሳን መላእክት የእመቤታችንን አስከሬን ወስደው በገነት አኑረውታል፡፡ በስምንተኛው ወር በነሐሴ አስከሬኗን እንደገና ከጌታ ተቀብለው በጸሎትና በምሕላ ቀበሩአት፡፡ በዚህ የቀብር ሥነ-ሥረዓት ላይ ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ ቶማስ አልነበረም፡፡ በተቀበረች በሦስተኛው ቀን እንደ ልጇ ተነስታ ስታርግ ፣ ቶማስ ከሀገረ ስብከቱ በደመና ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ ያገኛታል፡፡ በዚህ ጊዜ ትንሣኤዋን ሌሎች ሐዋርያት አይተው፣ ለእርሱ የቀረበት መስሎት ተናዶ፣ ‹‹...ፈቀደ ይደቅ እምደመናሁ፤ ከደመናው ለመውደቅ ተመኘ›› በፊት የልጅሽን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁ፡፡ አሁን ደግሞ ያንቺን ትንሳኤ ሳላይ ቀረሁ ብሎ ከደመናው ሊወረወር ቃጣው፡፡ በዚህ ጊዜ እመቤታችን ቶማስን አጽናናችው፡፡

አስደናቂው ሞት ፡፡ ድንግል ማርያም የአምላክ እናት ስትሆን ለምን አረፈች ?

 

 
ድንግል ማርያም የአምላክ እናት ስትሆን ለምን አረፈች ?
እግዚአብሔር ዘላለማዊ ኃይሉንና አምላክነቱን ለዓለም ከገለጸበት ታላቅ ሥራ መካከል በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም የገለጸው ድንቅ ሥራው በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛል፡፡ ይህንን ሁኔታ ድንግል ማርያም “ብርቱ የሆነ እርሱ ታላቅ ሥራን በእኔ አድርጓል ስለዚህም ምክንያት ፍጥረት ሁሉ ያመሰግኑኛል” ሉቃ.፩፥፵፱/1፥9/ በማለት ገለጸችው፡፡ ቅድሰት ኤልሳቤጥም የጌታዬ እናት” አለቻት /ሉቃ.፩፥፵፫/1፥43/ “መልአኩ ቅዲስ ገብርኤል ከሴቶች መካከል ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ” /ሉቃ.፩፥፳፰/1፥28/ አላት፡፡ ቅዱስ ዳዊት ልጄ ይላታል መዝ.፵፬፥፱/44፥9/ ሰሎሞን እኅቴ ይላታል /መኃ.፭፥፩/5፥1/ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስም እናት ሆና ተሰጠችው /ዮሐ.፲፱፥፳፮/19፥26/ ይህንን ድንቅ ሥራ ውስንና ደካማ የሆነ አእምሮ ሊገነዘበው ከሚችለው በላይ ነው፡፡
ቅዱስ አግናጢዎስ ዘአንጾኪያ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በጻፈው መልእክቱ እንደገለጸው” የቅድስት ማርያም ዘለዓለማዊ ድንግልና፤ አማኑኤልን መውለዷ፤ የማይሞተው ጌታ ሞት” እነዚህ ሦስቱ ከዚህ ዓለም ጥበበኞችና ገዢዎች የተሰወሩ ምሥጢራት ነበሩ፤ እነዚህ ድንቅ ምሥጢሮች በራሳቸው ከንግግርና ከቋንቋዎች ሁሉ በላይ ሁነው የሚነገሩ በእግዚአብሔር የዝምታ መጎናጸፊያ የተጠቀለሉ ድብቅና ጣፋጭ ምሥጢሮች ናቸው ይላል፡፡

Monday 10 February 2014

‹‹ጾመ ነነዌ እና የኮብላዊው ነቢይ የዮናስ ተግባር›› በፖፕ ሺኖዳ ሶስተኛ እንደተጻ

                                                                                                      ከሳምሶን ኃ/ሚካኤል

ነገ የሚገባው የነነዌ ጾም መቼም ለኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ከታላቁ ከጌታ ጾም በፊት  በእየአመቱ የሚጾም  ጾም  ነውና በደንብ ይታወቃል ይልቁን  አባቶቻችን እናቶቻችን ‹‹ የነይነይ ጾም›› አስከማለት ደርሰው  ስም አውጥተውላታል፡፡ ስያሜው ከጾመ ነነዌ ወደ ነይነይ  የተቀየረውበንባብ ተፋልሶ ይሁን  ወይም ቶሎ ቶሎ ነይ ለማለት ተፈልጎ …. በእርግጥ አላውቅም፡፡ ወደ ዋናው አሳቤ ስገባ..የብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሶስተኛ መጽሀፍ የሆነውን ስለ ነቢዩ ዮናስ የተጻፈውን ‹‹CONTEMPLATIONS ON THE BOOK OF JONAH THE PROPHET ›› የተባለውን መጽሀፍ ሳነብ ወዳጆቼስ ትንሽ ባካፍል ብዬ እንዲህ በውርስ ትርጉም አቀረብኩት፡፡

መጽሀፍ ቅዱሱ ታሪኩን እንዲህ ብሎ ይጀምራል…..‹‹የእግዚአብሔርም ቃል ወደ አማቴ ልጅ ወደ ዮናስ እንዲህ ሲል መጣ።ተነሥተህ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፥ ክፉታቸውም ወደ ፊቴ ወጥቶአልና በእርስዋ ላይ ስበክ።ዮናስ ግን ከእግዚአብሔር ፊት ወደ ተርሴስ ይኰበልል ዘንድ ተነሣ ወደ ኢዮጴም ወረደ፥ ወደ ተርሴስም የምታልፍ መርከብ አገኘ ከእግዚአብሔርም ፊት ኰብልሎ ከእነርሱ ጋር ወደ ተርሴስ ይሄድ ዘንድ ዋጋ ሰጥቶ ወደ እርስዋ ገባ።››ትንቢተ ዮናስ 11

1.  ‹‹ነቢዩ ዮናስ ራስ ወዳድ ነበር ››