ጥቅስ

ጌታዬ
እግዚአብሔር ሆይ
እስከዚህ ያደረስኸኝ
እኔ ማን ነኝ ?
ቤቴስ ምንድር ነው?
2 ሳሙ 7፥18

Tuesday 25 December 2012

አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫና ሥራዎቹ - ክፍል 1

 
ዜና ሕይወቱ ለአባ ጊዮርጊስ
ልደቱ
የወርቃማው ዘመን ወርቃማ ደራሲ፣ መናኝ፣ ጻድቅ፣ ሊቅ፣ የሕዝብ መምህር እና የሥነ ምሕንድስና ባለሙያ የሆነው አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ የተወለደው በ03፻፶7 ዓመተ ምሕረት በወሎ ክፍለ ሀገር በዛሬው ቦረና በጥንቱ ወለቃ ወረዳ ሸግላ በተባለ ቦታ ነው፡፡ አባቱ ሕዝበ ጽዮን እናቱ እምነ ጽዮን ይባላሉ፡፡ ስለ አባቱ ሕዝበ ጽዮን ሁለት የተለያዩ ታሪኮች ይተረካሉ፡፡ የሰኔ ድርሳነ ዑራኤል ምንባብ አባቱ በመጀመሪያ የትግራይ በማስከተል የሰግላ /ጋሥጫ/ አገር ገዢ እንደነበር ይወሳል፡፡ ገድሉ ደግሞ /ጠቢብ ወማእምረ መጻሕፍት ወአቡሁኒ መፍቀሬ እግዚአብሔር አምኁልቈ ካህናተ ደብተራ ዘውሳጤ ዓጸደ ቤተ ንጉሥ/ አባቱም የእግዚአብሔር ወዳጅና በቤተ መንግሥት በነበረችው ድንኳን /ሥዕል ቤት/ ከሚያገለግሉ ካህናት ወገን ነበረ ይላል፡፡ እንደ ገድሉ ገጸ ምንባብ ትርጉም ሕዝበ ጽዮን ከንጉሡ ሥዕል ቤት በቅዳሴ ወይም በማሕሌት ከሚያገለግሉ ካህናት አንዱ ነው፡፡ /. . . ወእሙኒ እም ሥዩማነ ወለቃ/ እናቱም ከወለቃ ሹማምንት ወገን ነች ይላታል፡፡ ይኸውም የጥንቱ ወለቃ /የዛሬው ደቡብ ወሎ፣ ቦረና ከላላ/ ከነበሩ መኳንንት ወገን መሆኗን ያመለክታል፡፡ የአባ ጊዮርጊስ ወላጆች ልጅ ሳይወልዱ ለረጅም ዓመታት ቆይተዋል፡፡ የልጅ ፍላጎታቸው እንዲሠምር ለሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ተሳሉ፡፡ ስእለታቸውም ሥምሮ በመልአኩ ቀዱስ ዑራኤል አብሣሪነት ወንድ ልጅ ወለዱ፡፡ ልጃቸውን ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስን በመማጸን ስለወለዱ ስሙን ጊዮርጊስ ብለው ጠሩት፡፡ ወላጆቹ የታላቁን ሰማዕት ስም ለልጃቸው ያወጡት ወደ ፊት በዓላውያን ነገሥታት ፊት ምስክር፣ አፅራረ አምነትን አሳፋሪ፣ ካህናትንና ምእመናት በየዘመናቱ ከሚነፍሱ የኑፋቄና የክህደት ነፋሳት በወንጌል ብርሃን ነፃ የሚያወጣ ሲሉ ይህን ስም እንዳወጡለት ድርሳነ ዑራኤል እንዲህ ይተርካል፡፡ ‹‹ዘይከውን መምህረ ኵሉ ዓለም ወበጸሎቱ ዘያድኅን አሞተ ሲኦል ፍቁረ ድንግል ማርያም ወላዲቱ ለአማኑኤል፡፡ ወመገሥጾሙ ለነገሥት፡፡ ወፀሮሙ ለዐላውያን ሃይማኖት በሰይፈ ቃሎሙ ለሐዋርያት ዘያጠፍኦሙ እም ብሔረ ኢትዮጵያ፤ ወለካህናተ ጽድቅ ዘይመርሆሙ እምጽልመተ ኑፋቄ መንገለ ብርሃን ቃለ ወንጌሉ ለክርስቶስ በትምህርተ ሕጎሙ ለሐዋርያት›› ይላል፡፡

ትምህርት
አባ ጊዮርጊስ የመጀመሪያ ደረጃ መንፈሳዊ ትምህርቱን ከወላጅ አባቱ ሕዝበ ጽዮን እንደተማረ ይገመታል፡፡ አባቱ የመጀመሪያ ደረጃ ተምህርቱን ካስተማሩት በኋላ መዐርገ ዲቁና እንዲቀበል ማድረጋቸውን ገድሉ ይነግረናል፡፡ ወሶበ ልህቀ ሕቀ ወሰዶ ኀበ ጳጳስ ወሴሞ ዲያቆነ፡፡ ባደገም ጊዜ ከጳጳስ ዘንድ ወሰደው ጳጳሱም በዲቁና አሾመው ይላል ገድሉ፡፡ ዲቁና መቀበሉን እንዲ መዓርገ ዲቁና የሰጡትን ጳጳስ ስም አይገልጽም፡፡ ዳሩ ግን መዓርገ ዲቁናን በ03፻፵1 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እስከ ዐፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት መጀመሪያ አካባቢ ከነበሩት ብፁዕ አቡነ ሰላማ መተርጉም እንደተቀበለ ይገመታል፡፡
መዓርገ ዲቁና ከተቀበለ በኋላ የአባ ጊዮርጊስ ወላጆች ለታላቅ ሐላፊነት የተመረጠውን ልጃቸውን በዘመኑ የታወቀ የነገረ ሃይማኖት ትምህርት ሊያስተምሩት ለሚችሉ መምህራን መስጠት እንዳለባቸው ወሰኑ፡፡ በወቅቱ ጥልቀት ያለው የነገረ ሃይማኖት ትምህርት ለመማር የሚመረጠው ትምህርት ቤት ሐይቅ እስጠፋኖስ ነበር፡፡ወደ ሐይቅ እስጢፋኖስ በዐፄ ዳዊት /03፻፷5 - 03፻፺5/ ዘመነ መንግሥት እንደገባ ገድሉ ይገልጣል፡፡ ሐይቅ እስጢፋኖስ የተለያየ ሊቃውንት የሚገኙት፣ በብዙ መጻሕፍት የተሞላውና ዙሪያውን በሐይቅ በመከበቡ የተማሪን ሐሳብ ለማሰባሰብ አመቺ የሆነ ቦታ ነው፡፡ አባ ጊዮርጊስ በሐይቅ እስጢፋኖስ ትምህርት አልገባው ብሎ ለሰባት ዓመታት ተቀምጦ ነበር፡፡ የትምህርት ቤት ሕይወቱም ከቅዱስ ያሬድ ይመሳሰላል፡፡ ቀዱስ ያሬድ ትምህርት አልገባው ብሎ ሰባት ዓመት እንደተቸገው እንደዚሁ አባ ጊዮርጊስም አብረውት የሚማሩት ተማሪዎች ይህ ትምህርት የማይገባው ስለ ምንድን ነው? በእርሱ ኃጢአት ነው ወይስ በወላጆቹ? ብለው እስከ ሚጠይቁ ድረስ ትምህርት አልገባ ብሎት ነበር፡፡ በዚያ ጊዜ የሐይቁ መምህር የነበረው ዐቃቤ ሰዓት ሠረቀ ብርሃን ለአባቱ ‹‹ልጅህ ትምህርት አይገባውምና የቤተ መንግሥት ነገር አስተምረው›› ብሎ መለሰው፡፡ አባቱ ሕዝበ ጽዮን ግን ‹‹ አንድ ጊዜ ለእግዚአብሔር ሰጥቼዋለሁ አልቀበልህም እዚያው ገዳሙን ያገልግል›› ብሎ እንደገና ላከው፡፡በዚህ ዓይነት መምህሩ ወደ ሐይቅ እስጢፋኖስ መልሶ ወሰደውና በጥበብ እድ ሥራ ላይ ተመደበ፡፡ በጥበበ እድ ባከበተው ዕውቀትም እንደ ቅዱስ ላሊበላ ከዐለት ፈልፍሎ ቤተ ክርስቲያን ለማነጽ ችሏል፡፡ ዛሬ ከዘመን ርዝማኔ የተነሣ ጥገና ባይደረግለትም አባ ጊዮርጊስ ፈልፍሎ ያሠራው ዋሻ ቅኔ ማኅሌት፣ ቅድስት እና መቅደስ ያለው ቤተ ክርስቲያን ብዙ የትሩፋት ሥራ በሠራበት በጋሥጫ ገዳም ይገኛል፡፡ የወለቃን ወንዝ ለመሻገር ያገለግል ዘንድ ከዓለት ፈልፍሎ የሠራው ድልድይም የሥነ ምሕንድስና ሙያው የታየበት አሻራ ነው፡፡አባ ጊዮርጊስ ዕውቀት ስለ ተሠወረው ሁል ጊዜ በሥዕለ ማርያም ሥር እየተንበረከከ ይጸልይ ነበር፡፡ የሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳምንም እህል በመፍጨት ያገለግል ነበር፡፡ አባ ጊዮርጊስ ይፈጭበት የነበረው የድንጋይ ወፍጮ አሁንም በገዳሙ ውስጥ ይገኛል፡፡ አንድ ቀን እመቤታችን ተገለጠችለትና አይዞህ ዕውቀት የተሠወረብህ ትምህርት ስለማይገባህ ሳይሆን የእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ እንዲገለጥ ነውና ታገሥ አለችው፡፡ ከዚያም ጽዋዐ ልቡና አጠጣችው፡፡ከዚህ በኋላ በሐይቅ እስጢፋኖስ ትምህርቱን በሚገባ ተምሮ አጠናቀቀ፡፡ በዕውቀቱም ቀድሞ የሚያውቁት ሁሉ ይደነቁበት ጀመር፡፡
አባ ጊዮርጊስ የያሬድንም ዜማ ተምሯል፡፡ የተማረውም ከአቡነ ሳሙኤል ዘጋርማ እንደሆነ ገድሉ ይገልጣል፡፡ ሊቁ በዚያ መን በዐፄ ዳዊት አማካኝነት በሰሜን ኢትዮጵያ የያረድ ድጓ ዋና ማዕከል በሆነው በደብረ ነጎድጓድም ተሹሞ አስተምሯል፡፡ ምክንያቱም በኢትዮጵያ የድጓ ሊቃውንት ዝርዝር አባ ጊዮርጊስ ይጠቀሳልና፡፡ በትርጓሜ መጻሕፍትና በቅኔ የጠለቀ ዕውቀት እንዳለውም ድርሰቶቹ ይመሰክራሉ፡፡የማስተማር ሥራውን የጀመረው በዚያው በሐይቅ እስጢፋኖስ መሆኑን ገድሉ በሚከተለው መልኩ ይገልጠዋል፡፡ ‹‹ወአብርሃ ለቤተ ክርስቲያን እንተ ተሐንጸት በሐይቅ ባሕር፣ ወእመ አምሃ አኀዙ ይስእሉ አምኀቤሁ ኵሎሙ ሰብአ ሀገር ቃለ መጻሕፍት ወትርጓሜሆሙ፣ ወኵሉ ቃለ ማሕሌት፤ በሐይቅ የታነጸችውን ቤተክርስቲያን እንድታበራ አደረጋት /አደመቃት/ ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከእርሱ ዘንድ የአገሪቱ ሰው ሁሉ የመጻሕፍትን ቃል ትርጓሜና ሁሉንም የማሕሌት ቃል ይጠይቁ ጀመር፡፡ ››ከሐይቅ በኋላ በዚያ ዘምን ሸግላ በመባል ትጠራ ወደ ነበረችው ወደ ትውልድ ሀገሩ ወደ ጋሥጫ ተጓዘ፡፡ በዚያ ጊዜ የነገሥታቱ መቀመጫ በዚያ የነበረ ይመስላል፡፡ ለዚህ ሦስት ምልክቶች አሉ፡፡ የመጀመሪያው በነገሥታቱ መቀመጫ አካባቢ አብያተ ክርስቲያናት እንደሚገዙት ሁሉ /አክሱምን፣ ላስታን፣ ጎንደርን፣ አንኮበርንና አዲስ አበባን በምሳሌነት ማንሣት ይቻላል፡፡/ በጋሥጫም በዚያ ዘመን ብዙ አብያተ ክርስቲያናት ነበሩ፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በገድሉ ላይ አባ ጊዮርጊስ ወደ ሽግላ በመጣ ጊዜ ወደ ቤተመንግሥት እንዳስገቡት የሚገልጥ ታሪክ መኖሩ ነው፡፡ ሦስተኛው መረጃ ጋሥጫ የዐፄ ይስሐቅ የክረምት ጊዜ ማረፊያ እንደነበረች ገድሉ መግለጡ ነው፡፡አባ ጊዮርጊስ ወደ ሽግላ ሲመጣ አባቱ በጣም አርጅቶና መንኩሶ ነበር፡፡ ስለዚህም በአባቱ እግር ተተክቶ በቤተመንግሥት ያለችውን ሥዕል ቤት እንዲያገለግል ወደዚያው አስገቡት፡፡ አባ ጊዮርጊስ በቤተመንግሥቱ የንጉሡን ልጆች ከማስተማሩም በላይ በቤተ መንግሥቱ ዙርያ ከነበሩት ሊቃውንት መካከል አንዱ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ግብፃዊው ጳጳስ አቡነ በርተሎሜዎስ ሥላሴን አንድ ገጽ ብለው ያምናሉ፡፡ ተብለው በተከሰሱ ጊዜ ነገሩን እንዲያጣሩ ከተመረጡት ከቄስ ሐፄ ተከሥተ ብርሃንና ከሐይቁ መምህር ከዐቃቤ ሰዓት ዮሴፍ ጋር አብሮ ተልኮ ነበር፡፡ እነዚህ ሦስት አበው ጳጳሱን ካነጋገሩ በኋላ ክሱ ሐሰት መሆኑን በማረጋገጥ ስለ ምሥጢረ ሥላሴ የሚገልጠውን የጳጳሱን እምነት በጽሑፍ ይዘው መጡ፡፡በቤተ መንግሥቱ በነበረ ጊዜ የንጉሡን ልጆች ይስሐቅን፣ ቴዎፍሎስን፣ እንድርያስን፣ ሀብተ ኢየሱስን፣ ሕዝቅያስን፣ ኢዮስያስን፣ ዘርዐ ያዕቆብንና ሴት ልጁን ዕሌኒን በምግባርና በሃይማኖት ቀርጿቸዋል፡፡ ወደ ዙፋን ከመጡት ቴዎድሮስ፣ ይስሐቅ፣ ዘርዐ ያዕቆብና እንድርያስ በስተቀር ሌሎች ታዋቂ አይደሉም፡፡ በእነዚህም የአባ ጊዮርጊስ የሕይወት ፍልስፍና ተንጸባርቋል፡፡ ዘርዐ ያዕቆብ በድርሰቱ ሲመስለው ቴዎድሮስ ደግሞ ለቅድስና ማዕረግ በቅቶ በሕይወት መስሎታል፣ በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ተብሎ ጽላት ተቀርፆለታል፣ በዓሉ ሰኔ ፳9 ቀን ይከበራል፡፡ ይስሐቅም በዘመኑ ፖለቲካዊና ባህላዊ እመርታ አሳይቷል፡፡… ይቀጥላል
ምንጭ ፡- መጽሐፈ ምሥጢር
ተርጓሚ፡- መምህር ኃይለ ማርያም ላቀው

No comments:

Post a Comment