ጥቅስ

ጌታዬ
እግዚአብሔር ሆይ
እስከዚህ ያደረስኸኝ
እኔ ማን ነኝ ?
ቤቴስ ምንድር ነው?
2 ሳሙ 7፥18

Sunday 23 December 2012

የቅዱስ መስቀሉ መቀበር

ሰገደ ጢስ (ጢስ ሰገደ)
ልዑል እግዚአብሔር ኃይሉንና ድንቅ
ሥራዎቹን ከሚገልጽባቸው ሥነ ፍጥረቶቹ
መካከል አንዱና ዋነኛው ራሱ ጌታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ዕፀ መስቀል
ነው፡፡ ዕፀ መስቀሉ ጌታችን ክብር ምስጋና
ይድረሰውና በደል ሳይኖርበት ዓለምን ለማዳንና
የሰውን ልጅ ሁሉ ከኃጢአትና ከበደል ነፃ
ለማድረግ ሲል እንደ በደለኛ ከአመፀኞች
ጋራ ተቆጥሮ አይሁድ በግፍ በሰቀሉት ጊዜ
ክቡር አካሉ ያረፈበትና እጅ እግሩ በችንካር
ጎኑ በጦር ተወግቶ ደሙ የፈሰሰበት
በመሆኑ ከዕፅዋት ሁሉ የላቀ ክብርና ሞገስ
ያለው ቅዱስ ነው፡፡
ስለሆነም የክብር ባለቤት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በክቡር ደሙ ያከበረው በቅዱስ ሥጋው የቀደሰውና መለኮታዊ ኃይሉና ባሕርያዊ ሕይወቱ ያረፈበት ሰለሆነ ኃይልን ሕይወትን ፈውስን ጽናትን የሚሰጥ ሆኖ በገቢረ ተአምርነቱ እየተገለጸና እየታወቀ በመሄዱ መስቀል የእግዚአብሔር ኃይልና የጥበቡ መገለጫ ነው፡፡ ጌታ ከትንሣኤውና ከዕርገቱ በኋላ ድውዮችን በመፈወስ ሙታንን በማስነሳት አንካሶችንና ዕውሮችን በማዳን ተአምራቱንና ኃይሉን መግለጽ የጀመረውም በቅዱስ መስቀሉ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ የዳኑትና ይህን ድንቅ ተአምር የተመለከቱ ሁሉ ሕይወትና ቤዛ የመሆን ጸጋ የተሰጠው መሆኑን እያመኑ መስቀል ኃይላችን መስቀል ቤዛችን መስቀል የነፍሳችን መድኃኒት ነው እያሉ የጸጋና የአክብሮት ስግደት የሚሰግዱለት ሁነዋል፡፡
የቅዱስ መስቀሉ መቀበር
Meskelአይሁድ ግን ቅዱስ መስቀሉ በፊታቸው ልዩ ልዩ ተአምራትንና ብዙ ምልክቶችን ሲያደርግ እያዩ ማመን ተሳናቸው ቀደም ሲል ጌታ በመካከላቸው በሕይወት /በአካል/ እየተመላለሰ በሽተኞቻቸውን እየፈወሰ ሙታኖችን እያስነሳና ኅብስት አበርክቶ እየመገበና ብዙ ተአምራት እያደረገ ቢያስተምራቸው ቀንተው ተመቅኝተው ገርፈውና ሰቅለው እንደገደሉት ሁሉ ይህንም ቅዱስ መስቀል ወደ ቆሻሻ ቦታ ከመጣላቸውም በላይ መሬት ቆፍረው ቀብረውት ነበር፡፡
አይሁድ ንጹሑን መስቀል በቆሻሻ ሲቀብሩ ከነጭራሹን ስመዝክሩ እንዲጠፋና ተረስቶ እንዲቀር ለማድረግ ከሁሉ በታች የጌታ መስቀልን አድርገው ሁለቱ ሽፍቶች ፈያታዊ ዘየማንና ፈያታዊ ዘጸጋም አብረው የተሰቀሉባቸው መስቀሎችንም አከታትለውና ደርበው ከቀበሩት በኋላ የከተማውን ቤት ጥራጊ ሁሉ በላዩ እንዲደፋ ዓዋጅ በማስነገር ተራራ እስኪያህል ድረስ በቆሻሻ ቁልል አስደፍነውት ነበር፡፡
በዚህ ዓይነት ከሁለት መቶ ዓመት በላይ ዘመን በማስቆጠርና ተከታታይ ትውልድን በማሳለፍ እየተረሳና ደብዛው እየጠፋ ከመሄድ በስተቀር የሚያስታውሰውና የሚያውቀው አልነበረም፡፡ አይሁድ ይህንን ማድረጋቸው ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ‹‹መስቀል መልዕልተ ኩሉ ነገር›› መሰቀል ከሁሉ በላይ ነው ሲል እንደተናገረው የማያቋርጥ የእግዚእብሔር ኃይል መገለጫ መሆኑን ባለመገንዘባቸው ነበር፡፡
ይሁን እንጂ ጌታ በቅዱስ ወንጌሉ ‹‹እስመ አልቦ ክዱን ዘኢይትከሰት ወአልቦ ኀቡዕ ዘኢይትዐወቅ›› የማይገለጥ የተከደነ የማይታወቅ የተሰወረ ምንም የለምና ሲል አስቀድሞ እንደተናገረው ሁሉ ማቴ 10.26 ሉቃ 12.2 ከሰው ኃይል ይልቅ የእግዚእብሔር ኃይል ከሰው ጥበብ ይልቅ የእግዚአብሔር ጥበብ ይበልጣልና እነሱ ተቀብሮና ተሸፍኖ /ተደፍኖ/ ይቀራል ያሉትን የእግዚአብሔር ኃይሉና ጥበቡ በሚገለጽባቸው ተአምራትና ምልክቶች የተሰወረ ተገልጦ እንዲወጣ ፈቃዱ በመሆኑ ለዚህ ምክንያት የሚሆኑትን ንጉሡ ቆሰጠንጢኖስና ቅድስት እሌኒን የቅዱስ መስቀልን ፍለጋ እና መገኘት ምክንያት አድርጎ አስነሳ፡፡
ቅድስት እሌኒ
እሌኒ
ቅዱስ መስቀሉን ፍለጋ
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ መስቀል ፍለጋ መነሻ ንጉሡ ቆስጠንጢኖስና እናቱ ቅድስት እሌኒ መሆናቸውን ታሪክ ያስረዳል፡፡ ታሪኩ ሲመረመርም ንጉሡ ቆስጠንጢኖስ አባቱ ቁንስጣ ይባላል፡፡ የበረንጥያ ሰው ሆኖ ብዙ ኅብረ ነገድ የነበረው በአንድ ወገን አረማዊ የነበረ ነው፡፡ እናቱ ቅድስት እሌኒ ግን የሮሀ ሰው አይሁዳዊት ነበረች ብሉይ ኪዳንና ሐዲስ ኪዳንን ተቀብላ ያመነች ክርስቲያን ነበረች፡፡ በዚህ ሁኔታ ልጇ ቆስጠንጢኖስን በጥበብ ሥጋዊና በጥበብ መንፈሳዊ እየተማረ እንዲያድግ ስለአደረገችውና ይበልጡን ደግሞ በመንፈሳዊ ኅብረ ጥበብ የጎለመሰ በመሆኑ በእናቱ የክርስትና እምነትና ባህል ጸንቶ ኖረ እናቱ ቅድስት እሌኒም ወደ ሀገሯ ወደ ኢየሩሳሌም ወሰደችው፡፡
ወደ ሀገሩ ቁስጥንጥንያ እንደተመለሰ ከ3ኛው መቶ ዓመተ ምሕረት ጀምሮ በነበረው ዘመነ ዲዮቅልጥያኖስና መክሲሚያኖስ የሚባሉ አላውያን ነገሥታት በሮም ሀገር ነግሠው በሚገዙት ዙሪያ ያሉትን አብያተ ክርስቲያናት እንዲያቃጥሉና በእነሱ ምትክ የጣዖት ቤቶች እንዲከፈቱ ክርስቲያኖችንም እንዲታረዱ ዓዋጅ የተነገረበት ክፉ ጊዜ ስለነበረ በቤተክርሰቲያንና በክርስቲያኖች ላይ መከራና ፈተና የደረሰበት ወቅት ነበር፡፡ በመሆኑም ቆስጠንጢኖስ ይህን በምዕመናኑ ላይ የደረሰውን ግፍ ተመልክቶ እንዴት ፍጡር ሆኖ በመሰሉ ፍጡር ላይ ይህን ያህል ይጨክናል እያለ ያዝንና ይቆረቆር ጀመር በዚህ ላይ እንዳለም ሌሊቱን በሕልሙ ራእይ ያያል፡፡
ወዲያውም አያይዞ ኒቁስጣኑ ኒቁስጣጣኑ የሚል ምልክት በጻፍጻፈ ሰማይ በሰሌዳ ብርሃን ተቀርጾ አየ በዚያ አካባቢ አውስግንዮስ የሚባል ሰው ነበረ ይህንንም ራእይ ተርጉምልኝ አለው፡፡ የበቃ ሰው ነበረና ይህ ያየኸው ራእይ የመሰቀል ምልክት ነው፡፡ ትርጉሙም በዚህ የመስቀል ምልክት ‹‹ትመውዕፀረከ መጸላዕተከ›› ደመኛህንና ጠላቶችህን ድል ታደርጋለህ ድል ትነሳለህ ማለት ነው፡፡ ብሎ ነግሮታል፡፡
ይህንም የመስቀሉን ኃይልና አሸናፊነትን ምሥጢር በሰማይ የብርሃን ሰሌዳ ተቀርፆ ምልክቱን እንዲያይ ያደረገው ባልደረባው መልአክ ቅዱስ ሚካኤል እነደሆነ በታሪክ ተጽፎ ይገኛል፡፡ ንጉሡ ቁስጠንጢኖስም ይህን የመስቀል ምልክት በየጦር ሠራዊቱ ደረት፤ በየፈረሱ አንገትና በየመሳሪያው ሁሉ እንዲያደርጉ ዓዋጅ አስነገረ፡፡
ከዚያ በኋላ ክተት ሠራዊት ነጋሪት ብሎ ዘመተባቸው፡፡ በዘመቻው ጊዜ በዲዮቅልጥያኖስና በመክሲሚያኖስ ላይ አድረው ደም ያፈስሱ የነበሩት አጋንንት በመስቀል ፊት መቆም አይችሉምና ድል ሆኑ እየተከተለም አጥፍቷቸዋል፡፡
ወዲያውም ሮም ገብቶ መንግሥትን በያዘ ጊዜ ከሞት ያመለጡትና በሕይወት የተረፋት ምዕመናን የመስቀሉንና የጻሕል ጽዋውን ስብርባሪ ይዘው መስቀል ኃይልነ መስቀል ጽንዕነ መስቀል መድኃኒትነ እያሉ ተቀበሉት፡፡
ከዚያም እናቱ ቅድስት እሌኒ ቀደም ሲል ልጄ ቆስጠንጢኖስን ወደ ክርስትና አምነት እንዲገባ ካደረክህልኝ ቅዱስ መስቀልህን አስፈልግልሃለሁ ብላ ተስላ ነበረና በተሳለችው መሠረት ሁሉንም ስለሰመረላት ወደ ኢየሩሳሌም ሂዳ ቅዱስ መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ ማፈላለግ ጀመረች፡፡
ታሪክ የሚያውቁ የአካባቢው የአይሁድ ሽማግሌዎችን እየጠየቀች ስታፈላልግ አዝቂረ ኪርያቅ /አረጋዊው ኪራኮስ/ የሚባሉትን ብዙ ገንዘብ እሰጣችኋለሁና የክርስቶስን ቅዱስ መስቀል የተቀበረበትን አሳዩኝ እያለች ብትዘበዝባቸው ኪራኮስ ይህ የሚታየው ታላቅ ተራራ ከ300 ዓመት በላይ ሆኖታል የከተማውን ጥራጊ የተከመረበት ሆኖ ይታያል፡፡ ቅዱሱ መስቀል በዚያ እንደተቀበረ አበው ይነግሩናል አላት፡፡
ነገር ግን ችቦው አሰብስበሽ ደመራን ደምረሽ ዕጣኑን ጨምረሽ እሳቱን አቀጣጥለሽ ብታጤሺው መስቀሉን ማግኘት ይቻል ይሆናል ብሎ ነገራት፡፡ እርሷም ጸሎቷን ወደ እግዚአብሔር ካቀረበች በኋላ አረጋዊው ኪራኮስ በአመለከታት መሠረት ዕጣኑን ጨምራ ደመራውን ብታቀጣጥለው የዕጣኑ ጢስ ወደ ሰማይ ወጥቶ ተመልሶ መስቀሉ ከተቀበረበት ተራራ ላይ ጢሱ ሰገደ በእጁ ጠቅሶ እንደማሳየት ያለ ነው፡፡
መስቀል
እንግዲህ እዚህ ላይ የምንመለከተው የጢሱን ስግደት ተአምራዊ ኃይልን ነው፡፡ በእርሱ እንደተገለጸው በሥነ ፍጥረት አድሮ በጢሱ ስግደት አንፃር የቅዱስ መስቀሉን ኃይልና ክብርን በመግለጽ ለጌታ ቅዱስ መስቀል የጸጋ ስግደትን መስገድና ማክበር እንደሚገባ ገልጾ ማመልከቱንና ማስተማሩን እናያለን፡፡
ይህም በራሱ የቅዱስ መስቀል ኃይልና አምላካዊ ጥበብ ስለሆነ እንደ ትልቅ ተአምር ነው፡፡ ጢስ ከዕጣን ቅታሬ ከእንጨት ትርኳሽና ከነዳጅ ሁሉ የሚወጣ ረቂቅ ነገር ሲሆን ከቅዱሳት መጻሕፍት እንደምንረዳው የልዩ ልዩ አምላካዊ ሥራዎች መገለጫና ማስፈጸሚያ ኃይልና ተልእኮ ያለው መሆኑ ይታወቃል፡፡
ምድርንም ‹‹የጌታን ቅዱስ መስቀል ቀብረሻልና ውለጅ›› ብትባል ‹‹አለ›› ብላ እውነቱን ከማውጣት በስተቀር ምክንያት አልፈጠረችም ጢሱ መስክሮባታልና፡፡ እግዚአብሔር አምላክ በረቂቅ ጥበቡ በፍጡር እያደረ በሚሠራው ድንቅ ሥራ በሚገልጸው ምሥጢር ምድርም የምታውቅ ምስክር ናትና ባወቀችው መመስከሯ ነው፡፡
ቅድስት እሌኒም የጢሱን ስግደት ተመልክታ ቅዱስ መስቀሉ ከዚህ ቦታ አለ ብሎ ሲጠቁመን ነው በማለት አለምንም ጥርጥር መሰከረም 17 ቀን 300 ዓ.ም አካባቢ ሠራዊቷንና ሕዝቡን አስከትላ ቁፋሮ አስጀምራ መጋቢት 10 ቀን በዚሁ በተገለጸው ዓ.ም ቅዱስ መስቀሉን ለማግኘትና ለማውጣት ችላለች፡፡
የተገኙት መስቀሎች አንዱ ጌታ የተሰቀለበት ሁለቱ ሽፍቶቹ ፈያታዊ ዘየማንና ፈያታዊ ዘጸጋም የተሰቀሉበት ሦስት ሲሆኑ የጌታን መስቀል ገና ሲያወጡት ቦግ ብሎ ብርሃን የፈነጠቀበትና አካባቢውን ያንፀባረቀ ከመሆኑም በላይ ዕውሮችን አብርቷል፡፡ ድውያኖችን ፈውሷል፡፡ አንካሶችን አቅንቷል፡፡ ሙታንንም አስነስቷል፡፡ በዚህ ገቢረ ተአምርነቱ የጌታ መስቀል መሆኑ ታውቋል፡፡
ቅድስት እሌኒም በዚህ ጊዜ ሐሳቧና ምኞቷ ስለተፈጸመ ደስ ብሏት እግዚአብሔርን አመሰገነች፡፡ ለመስቀሉም ሰገደች ተሳለመችውም በኢየሩሳሌም የነበሩ ምእመናን ሁሉ በቅዱስ መስቀል መገኘት ደስ ስለአላቸው አግዚአብሔርን አመስግነው ለመስቀሉ ሰግደዋል፡፡ ተሳልመውታልም ልዩ ልዩ ደዌና በሽታ የነበረባቸው ሰዎችም እየዳሰሱ ተፈውሰዋል፡፡
ቅድስት እሌኒም ይህን እግዚአብሔር ያደረገላትን ቸርነት ለልጇ ለንጉሡ ቆስጠንጢኖስ ላከችለት እሱም ሰምቶ ደስ ስለአለው ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ፡፡ ከዚያ በደረሰ ጊዜም አናቱ ቅድስት እሌኒና ሕዝቡ በአንድነት በዝማሬ ተቀበሉት የመስቀሉንም ሁኔታ ተረኩለት ንጉሡ ቆስጠንጢኖስም ቅዱስ መስቀሉ በተገኘበት ቦታ ቤተክርስቲያን በስሙ እንዲሠራ ፈቀደ ዕብነ መሠረትም አኑሮ ወደ መናገሻቸው ወደ ቁስጥንጥንያ ተመለሰ፡፡
በእናቱ በንግሥት እሌኒ አማካይነት ቤተክርሰቲያኑ ተሠርቶ መስከረም 16 ቀን ቅዳሴ ቤቱ ተከብሯል ወደ ጎልጎታ እንዲገባ ተደርጓል፡፡ በቦታው የነበሩ ጳጳሳትና ካህናቱም ሕዝቡም ተስማምተው ቅዳሴ ቤቱ በየዓመቱ መስከረም 16 ቀን እንዲከበር ሥርዓት ሠርተዋል፡፡
2ተኛም ሕርቃል የተባለው ንጉሥ በ628 ዓም በቁስጥንጥንያ ነግሦ በነበረ ጊዜ የፋርስ ሰዎች ወደ ኢየሩሳሌም ዘመቻ አድርገው ሕዝቡን አጥፍተው ከቤተልሔም በቀር ሁሉንም አብያተ ክርሰቲያንናት አቃጥለዋል፡፡ ቤተልሔምን አለማቃጠላቸው አባቶቻችን ሰብአሰገል ቀድሞ በጌታ ልደት እጅ መንሻ ያቀረቡበት የሰገዱበት ስለሆነ አትንኩ ተባብለው ሰለተውት ነው፡፡ ሕርቃልም ይህን ሰምቶ እጅግ አዝኖና ወዲያው ዘመቻ አድርጎ ለጊዜው መስቀሉን አላገኘውም፡፡ ምከንያቱም አንድ አዝማች መኮንን በጦርነቱ ጊዜ መስቀሉን ወስዶ በቤቱ አንፃር ጥልቅ ጉድጓድ አሰቆፍሮ ቀብሮት ነበርና፡፡
ነገር ግን መኮንኑ የማረካት የካህናት ወገን የሆነች በአጠገቡ ትኖር የነበረች አንዲት ሴት ሲቀብሩት አይታ ስለነበረ መርታ አሳየችው፡፡ ሂዶ ሠራዊቱን ይዞ ቢያስቆፍረው አገኘው ደስ ብሎት ሰገደለት ሳመውም ኤጲስ ቆጶሱና ካህናቱ አንድ ሁነው ንጉሡ ሕርቃልም በልብሰ መንግሥቱ መስቀሉን አጎናፅፎ በታላቅ ክብርና ደስታ ወደ ሀገሩ መልሶታል፡፡
ይዞት ሲመለስ የሰማ ሁሉ ከኢየሩሳሌም ጀምሮ እስከ ቁስጥንጥንያ ድረስ ችቦና ጧፍ እያበሩ ወንዱ በሆታ ሴቱ በእልልታ መስቀሉን እንደታቦት ተሸክመው ከተማውን በማዞር ጥንት በነበረበት ቦታ በጎልጎታ አኑረውታል፡፡
የግማደ መስቀሉ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት
ቅዱስ መስቀሉን ለማጥፋት አጽራረ መስቀል፣ ዓላውያን፣ ከሐድያን ያላደረጉት ሙከራና ጥረት አልነበረም፤ ይሁን እንጂ ቅዱስ መስቀል የእግዚእብሔር ኃይል ስለሆነ እነርሱ በመስቀሉ ኃይል ከሚጠፋ በስተቀር ቅዱስ መስቀሉን ማጥፋት አልተቻላቸውም፡፡
ስለሆነም አራቱ ፓትርያርኮች የሮም፣ የእስክንድርያ፣ የቁስጥንጥንያና የኤፌሶን ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ መስቀሉን በየሀገረ ስብከታቸው ለራሳቸው፣ ለሕዝባቸውና ለሀገራቸው ኃይልና ጽንዕ በረከትና ረድኤት ሰላምና ፍቅር እንዲሰጣቸው ተካፍለው ወደ የአህጉራቸው ሲወሰዱት ዋናውና መካከለኛው በኢየሩሳሌም እንደቀረ በአበው ይተረካል፡፡
ወደ ሀገራችን ወደ ኢትዮጵያ የመጣበት ምክንያትም በ14ተኛው ክፈለ ዘመን መጀመሪያ ነግሠው የነበሩት ዐፄ ዳዊት በሀገራችን ተደጋጋሚ ረሀብና በሽታ በሕዝባቸው ላይ እየደረሰ ስለአስቸገራቸው ወደ እግዚአብሔር አመለከቱ፤ በራእይ ችግሩ ሊወገድ የሚችለው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ግማደ መስቀል ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ የመጣ እንደሆነ ነው ሲል ገለጸላቸው፡፡
ንጉሡም መልእክተኞቻቸውን ልከው እንዲመጣ አድርገዋል፤ ስለሚኖርበት ቦታም ‹‹አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል›› ሲል በራእይ ገልጾላቸው ስለመስቀሉ ክብር ሲሉ ሱዳን ድረስ ሂደው ከመልእተኞቻቸው ቅዱስ መስቀሉን በክብር ተቀብለው በስናር በኩል ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ እስከዛሬ ድረስ የዳዊት ተራራ እየተባለ በሚጠራው ቦታ ላይ በድንገት በሞት ስለተለዩ በዚያው ተቀብረዋል፡፡
በኋላ ግን ግማደ መስቀሉ ከክብር አጽማቸው ጋር በልጃቸው በዐፄ ይስሐቅ አማካኝነት መጥቷል ፄ ይስሐቅም ከፍፃሜ ሳያደርሱት በሞት ስለተለዩ ወንድማቸው ዐፄ ዘርዓያዕቆብ ‹‹አንብር መስቀልየ በዲቦ መስቀል›› የሚለው ራእይ እንደ አባታቸው እንደ ዐፄ ዳዊት ተገልጦላቸው ከብዙ ማፈላለግ በኋላ በግሸን ደብረ ከርቤ እንዲያርፉ ተደርጓል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር
ምንጭ፡- 1. የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት 2003 ዓ/ም ለመስቀል ደመራ በዓል የተዘጋጀ ልዩ ዕትም መጽሔት
2. የሰ/ት/ቤቶች/ማ/መ/ማኅበረ ቅዱሳን ለመስቀል ደመራ በዓል የተዘጋጀ በራሪ ጽሑፍ
3. መዝገበ ታሪክ መጽሐፍ

No comments:

Post a Comment